ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የውጭ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ አቀረቡ

1086

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለኢንቨስትመንት የውጭ ባለሃብቶች መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ባለው የአለም የኢኮኖሚ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች ያለች አገር ናት።

ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው አለም ዓቀፍ ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ሊያፈሱ የሚችሉባቸው ሰፊ መልካም እድሎች እየተፈጠሩ በመሆኑ ባለሃብቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ለውጥ አገሪቱ እንድትረጋጋና ሰላማዊ እንድትሆን በማድረግ ላይ በመሆኑ ከውጪ የሚገባው ባለሃብት እንደልቡ ተዘዋውሮ ቢዝነስ ለመስራት የሚያስችለው መሆኑን አስረድተዋል።

የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እየተደረጉ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወጣቱን ተጠቃሚነትና ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ለማረጋገጥና የተሻለ የትምህርት ጥራት ለማምጣት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደቱ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲበረታቱና ያለባቸውን የገንዘብ አቅርቦት ለማስተካከል እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ቀድሞ የነበሩ ህጎችና ፖሊሲዎችን በማስተካከል አስቻይ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢንቨስትመንትና የንግድ አሰራር ኮዶችን በመስተካከል ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አገሪቱ የግል ዘርፉ የኢኮኖሚው ዋና አንቀሳቃሽ እንዲሆን በአብዛኛው በመንግስት ተይዘው የነበሩ ተቋማትን ወደ ግል ለማዞር በሂደት ላይ እንደምትገኝ አስታውቀዋል።

በዚህም አለም ዓቀፍ ኢንቨስተሮች በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በሎጂስቲክ፣ በኃይል፣ በበረራ ባባቡርና መሰል ዘርፎች እንዲሳተፉ መንግስት ፍላጎት ስላለው በር በመክፈት ላይ ይገኛል ብለዋል።

”ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት አገር በመሆኗ ከፍተኛ የገበያ መዳረሻ አገር ናት ይህ ደግሞ መዋለ ንዋይ ለማፍሰስ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል” ብለዋል።

ከዚህም ሌላ አገሪቱ ለአፍሪካ ዋና መቀመጫ መሆኗና የተለያዩ አለማቀፍ የኢኮኖሚ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ ለውጭ ባለሃብት ተጨማሪ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል።

የአለም ኢኮኖሚ ጉባኤ በየአመቱ በስዊዘርላንድ ዳቮስ የሚካሄድ ሲሆን የተጀመረው እ.አ..አ ከ1987 ጀምሮ ነው።