የአገሪቱ ስፖርት አስተዳደር ሥር-ነቀል ሪፎርም እንደሚያስፈልገው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ተናገሩ

420

አሶሳ ጥር 15/2011 ከስፖርት የሚፈለገውን አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት ዘርፉ ሥር-ነቀል ለውጥ እንደሚያስፈልገው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

የአገሪቱን ስፖርት ማሻሻል ዓላማው ያደረገ ክልሎች የተሳተፉበት የቪዲዮ ኮንፍረስ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሐብታሙ ሲሳይ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ፖሊሲው ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ዘርፉን በሚያለማ መልኩ በግልጽ የተቀመጠ ቢሆንም፤በሥራ ላይ በማዋል ረገድ ግን ችግሮች ይስተዋሉበታል።

ፖሊሲውን መነሻ በማድረግ ስፖርቱን ለማልማት ጥረት ቢደረግም፤ባለድርሻ አካላት ፖሊሲውን ተረድተው በመሥራት ችግሮች እንደሚታዩ አመልክተዋል፡፡

“የኢትዮጵያ ስፖርት አደረጃጀት ከ76 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ አገሪቱን የመሩ መንግሥታት ስያሜውንና ቅርጹ ለ12 ጊዜ ያህል በመቀያየር በስፖርቱ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የአገሪቱ አብዛኛዎቹ ስፖርት የሚከናወነው በቀበሌዎች ቢሆንም፤ አደረጃጀቱና ባለሙያዎች ያሉት በወረዳና ከዚያ በላይ ባሉ መዋቅሮች መሆኑ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

ስፖርቱን የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው ስፖርት ምክር ቤቶችና ፌዴሬሽኖች ቁመናቸው አለመጠናከር፣በተለይም  በበጀትና በሰው ኃይል አለመሟላት ዘርፉ ዕድገት እንዳይመዘገብ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በፌደራልና በክልሎች መካከል የተናበበ አደረጃጀት አለመኖርና የስፖርት ምክር ቤቶች ጉባዔ ወቅቱን ጠብቆ አለመካሄድም ችግሮች እንደሆኑ  ጠቁመዋል፡፡

ኪራይ ሰብሳቢነትም ሌላው በዘርፉ ችግር እንደሆነ አቶ ሐብታሙ  ገልጸዋል፡፡

የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች የራሳቸው ካርታ የሌላቸውና ቁጥራቸውም አነስተኛ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣አንዳንዴም ማዘውተሪያ ቦታዎቹ ለባለሃብቶች፣ ለጋራና ለግል መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሲሰጡ እንደሚስተዋል ተናግረዋል፡፡

ስፖርቱን ሕዝባዊ መሠረት ባለመያዙ አብዛኛዎቹ የብሔራዊና ፕሪሚዬር ሊጎች እግር ኳስ ቡድኖች በመንግሥት በጀት እንደሚንቀሳቀሱ በአብነት አቅርበዋል፡፡

ተተኪ ስፖርተኞች ዋነኛ መፍለቂያ በሆኑት ትምህርት ቤቶች ያለው እንቅስቃሴና በሥራ ቦታ ስፖርትን ለማስፋፋት የሚደረገው እንቅስቃሴ በሚፈለገው ልክ ስላልሆነ  ትኩረት ለያገኝ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትር ዴታው ገለጻ ችግሮቹ በየስፖርት ዓይነቶች ጠንካራ ክለቦችና አገርን የሚወክሉ ቡድኖችን ለማፍራት በሚደረገውን ጥረት ላይ ተጽእኖ አሳድረዋል፡፡

የአገሪቱን ስፖርት ከሌሎች አገሮች ደረጃ በማድረስ ከዘርፉ የሚፈለገውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማግኘት በቅርቡ በበርካታ የፌደራል ተቋማት የታየው ለውጥ በስፖርቱም ዘርፍ ሊደረግ እንደሚገባ አቶ ሃብታሙ አስገንዝበዋል፡፡

“ስፖርት ሠላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ነው”  የሚሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት የአጭርና ረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ አስቀምጦ መተግበር ይገባል ብለዋል፡፡

“የስፖርት ጉዳይ የዘርፉ አስፈጻሚ አካላት ብቻ ተደርጎ የሚታየው አካሄድ ተቀይሮ ኅብረተሰቡን ጨምሮ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ጭምር በባለቤትነት መሳተፍ አለባቸው” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የስፖርት ምክር ቤቶች፣ ክለቦች፣ ማህበራት ሌሎችም ባለፈው አፈጻጸማቸውን እንዲፈትሹ አሳስበዋል፡፡

ስፖርታዊ ጨዋነት ለመመለስ  ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡

“ስፖርቱን ለማሻሻል ችግሮቹን ከነ-መፍትሔያቸው ማንሳት ሲገባቸው የውጭ ስፖርት ላይ ያተኮሩ መገናኛ ብዙኃን እይታቸውን አገራዊ ስፖርት በማሳደግ ላይ ማድረግ አለባቸው” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚሁ አገር አቀፍ የቪዲዮ ኮንፈረንስ ክልሎች ተሳትፈዋል፡፡