ፍርድ ቤቱ በአቶ ቴዎድሮስ አዲሱ ላይ ክስ ለመመስረት የሰባት ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ

66

አዲሰ አበባ  ጥር 15/2011 ዐቃቤ ህግ በአቶ ቴድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ላይ ክስ ለመመስረት የሰባት ቀናት ጊዜ ቀጠሮ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተፈቀደ።

አቶ ቴድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) በሶማሌ ክልል ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. በነበረው ሁከት እጃቸው አለበት ተብለው ተጠርጥረው ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

ተጠርጣሪው በክልሉ በተቀሰቀሰው ሁከት 'ሂጎ' በሚል ስያሜ የሚታወቀውን ቡድን በማነሳሳትና ሁከቱን የሚያባብስ ቲ-ሸርት በማደል በድርጊቱ እንደተሳተፉ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ማቅረቡ ይታወሳል።

መርማሪ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ የሚያደርገውን ምርመራ አጠናቆ ጥር 8 ቀን 2011 ዓ.ም መዝገቡን ለዐቃቤ ህግ ማስረከቡን ለፍርድ ቤት ገልጿል።

በዚህ መስረትም ዐቃቤ ሕግ ክስ ለመመስረት የዘጠኝ ቀናት ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው የጠየቀ ቢሆንም መዝገቡን ቀድሞ በመረከቡ በሰባት ቀናት ጊዜ ውስጥ የክስ መመስረቻውን እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዚሁ መሰረት ዐቃቤ ህግ የክስ መመስረቻ መዝገቡን ለጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም