አመራሩ ለህብረተሰቡ ፍላጎት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

843

አሶሳ ጥር 15/2011 በቅርቡ የተዋቀረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካቢኔ ለህብረተሰቡ ፍላጎት በመስራት ሀገራዊ ለውጡን እንዲያጠናክር የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ እያንዳንዱ ካቢኔ የ100 ቀናት ተግባራዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ወደሥራ ሊገባ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ገዥው ፓርቲ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቤጉህዴፓ) በቅርቡ ባደረጉት አስቸኳይ ጉባኤ የተለያዩ የአመራር ሹመቶች መሰጠታቸው ይታወሳል፡፡

አንዳንድ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ክልሉ ከራሱ አልፎ ለሀገሪቱ የሚውል እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት ነው፡፡

የተፈጥሮ ሃብቱን በሚገባ አልምቶ የህብረተሰቡን ኑሮ በመቀየር በኩል የክልሉ መንግስት ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡

አቶ ሰይድ አደም የተባሉ የከተማው ነዋሪ እንዳሉት ከዚህ ቀደም አብዛኞቹ የክልሉ አመራሮች የህዝብን ፍላጎት በማዳመጥ በኩል የነበራቸው ልምድ አነስተኛ ነው፡፡

ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ሲያስቀድሙ እንደነበረም ተናግረዋል፡፡

በቅርቡ የተዋቀረው የክልሉ መንግስት ካቢኔ አባላትም አብዛኞቹ ለረጅም ጊዜ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በመስራት ልምድ ያላቸው መሆኑንም አቶ ሰይድ ተናግረዋል፡፡

” ከክልሉ የካቢኔ አባላት አብዛኞቹ ባይለወጡም የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ይደግፋሉ የሚል ተስፋ አለኝ ” የሚሉት አስተያየት ሰጪው የካቢኔ አባላት ለህብረተሰቡ ፍላጎት በመስራት ሀገራዊ ለውጡን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በተለይ ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ጋር ተቀራርበው በመወያየት የህብረተሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ሥራ ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አብዱራዛቅ አህመድ በበኩላቸው በቅርቡ አሶሳ ከተማን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው ግጭት ተወግዶ ክልሉ እየተረጋጋ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

“የክልሉ ህዝብ ዋነኛ ፍላጎት ሠላም እና ልማት ነው” የሚሉት አስተያየት ሰጪው ለእዚህም አመራሩ ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡ ሃሳብ በመስጠት የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

በቅርቡ የተሾሙ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ህብረተቡን በቅርበት በማወያየት ለህዝብ ፍላጎትና ለሀገራዊ ለውጥ እንዲሰሩም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡

ህብረተሰቡ የተለመደውን ድጋፍ ከማድረግ እንደማይቆጠብ አስተያየት ሰጪው ጠቁመዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የክልሉ ህዝብ የሚያነሳቸውን በርካታ ጥያቄዎች ለመመለስ ካቢኔውን ከ18 ወደ 14 ዝቅ እንዲል መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

እያንዳንዱ የካቢኔ አባል የህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ከሃገራዊ ለውጡ አንጻር መመለስ የሚያስችለው የ100 ቀናት የሥራ ዕቅድ ማዘጋጀቱንና በጥቂት ቀናት ውስጥ ወደተግበራ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

በዕቅዱ አተገባበር ላይ ጠንካራ ክትትል እንደሚደረግ ጠቅሰው ውጤት የሚያመጡ የካቢኔ አባላት የተሻለ እውቅና ሲሰጣቸው ውጤት ያላመጡትም ተጠያቂ እንደሚሆኑ አመልክተዋል፡፡

” በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ለማምጣትም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እንደሚሰራ አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደሚሉት በክልል አሁን ያለው የመንግስት ተቋማት አደረጃጀት ያለውን ውስን በጀት፣ የሰው ኃይል እና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም በሚያስችል መልኩ የተዋቀረ ነው፡፡

“በሀገሪቱ ያለውን ለውጥ በክልሉም ማስቀጠል የሚቻለው የነበረውን አመራር በሙሉ በአዲስ መተካት ሳይሆን በአዲስ አስተሳሰብ በጋራ ለክልል ብሎም ለሃገር ልማት መነሳት ሲቻል ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በክልሉ እስከወረዳ ያለው አብዛኛው መዋቅር በወጣት አመራር መዋቀሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ አመልክተዋል።

“በክልሉ በሚከናወኑ የልማት ዕቅዶች ህብረተሰቡ ዋነኛ አጋዥ እንዲሆን ይደረጋል” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ፓርቲውንም ተሳታፊ ለማድረግ ዕቅድ መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡