አምቡላንስ በማጣት በቤታችን ለመውለድ ተገደናል-- እናቶች

64

ደብረብርሀን ጥር 15/2011 ወደ ጤና ተቋም የሚደርሱበት  አምቡላንሰ በማጣት በቤት ውስጥ በባህላዊ መንገድ ለመውለድ መገደዳቸውን በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ እናቶች ተናገሩ።

በዞኑ የሲያ ደብርና ዋዩ ወረዳ የወሌ ደነባ የቀበሌ  ነዋሪ  ወይዘሮ  ዘርፌ ንጉሴ ለኢዜአ እንዳሉት  ቀደም ሲል ሁለት ልጆቻቸውን በጤና ተቋም በመውለዳቸው የፀና ህመም  ሆነ የከፋ ደም መፍሰስ አላጋጠማቸውም ነበር።

ሶስተኛ ልጃቸውን ለመውለድ መጸነሳቸውን  ካረጋገጡበት ጊዜ ጀምሮ ለነፍሰ ጡር እናቶች የሚሰጠውን የቅድመ ወሊድ ህክምና ደነባ ሆስፒታል  ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

ድንገተኛ ምጥ ሲጀምራቸው የአምቡላስ አገልግሎት ማግኝት ባለመቻላቸው በመኖሪያ ቤታቸው ለመውለድ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በሲዳበርና ዋዩ ወረዳ የጋሻምባ ቀበሌ  ነዋሪ ወይዘሮ ፉርኖ ብርቅነህ  በበኩላቸው የመጀመሪያ ልጃቸውን ለመውለድ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የአምቡላንስ አገልግሎት ቢጠይቁም ባለማግኘታቸው ቤት ውስጥ መውለዳቸውን ተናግረዋል።

ከሶስት ቀናት ተከታታይ ህመም በኋላ በተፈጥሮ ምጥ  መውለዳቸውን ያመለከቱት ወይዘሮ ፉርኖ "  በየዓመቱ በምንከፍለው 160 ብር የጤና መድን ዋስትና የምንፈልገውን አገልግሎት እያገኘን አይደለም" ብለዋል።

አሁን ላይ የአራት ልጆች እናት መሆናቸውን የገለጹት የኤጀርሳ ቀበቲ ቀበሌ ነዋሪ  ወይዘሮ ትርፌ እንግዳ በበኩላቸው አራተኛ ልጃቸውን አምቡላንስ ባለማግኘታቸው በመኖሪያ ቤታቸው መውለዳቸውን አስረድተዋል።

የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዋ ወይዘሪት ሰብለ ተስፋ እናቶች የቅድመ ወሊድ የህክምና ክትትል ቢያደርጉም የመወለጃ ጊዜያቸው  የደረሱ እናቶችን ተከታትሎ በሰለጠነ የጤና ባለሙያ እንዲወልዱ በወረዳ አመራር በኩል የሚደረገው ድጋፍ ዝቅተኛ መሆኑን አመለክተዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በወረዳው 112 የሚሆኑ እናቶች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ መውለዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት እጅጋየሁ ተሰማ ናቸው፡፡

ከእነዚህም 22 የሚሆኑ እናቶች በአምቡላንስ እጥረት በቤታቸው እንደወለዱ መረጋገጡን ተናግረዋል።

በወረዳው ካሉት ሦስት አምቡላንሶች መካከል ሁለቱ በብልሽት በመቆማቸው በአንድ አምቡላንስ ብቻ አገልግሎቱን በመሰጠቱ የችግሩ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጥበቡ አበራ በበኩላቸው አንድም እናት በባህላዊ መንገድ በቤት ውስጥ እንዳትወልድ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ጥረት ቢደረግም ማሳካት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው ግማሽ የበጀት ዓመት 36 ሺህ 200 እናቶች  በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ለማድረግ ታቅዶ 17 ሺህ እናቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ሆኖም 942 እናቶች ደግሞ በቤት ውስጥ በባህላዊ መንገድ መውለዳቸውን አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት በቤት ውስጥ የወለዱት እናቶች ቁጥርም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር  ሲነፃፀርም በ233 እናቶች ጭማሪ አሳይቷል፡፡

የዞንና የወረዳ የጤና አመራሩና ባለሙያው እንዲሁም የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች የቅንጅት መጓደልና ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ለችግሩ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩን ለመፍታት በጤና ተቋማት የተቋቋሙ 92 የእናቶች ማቆያ ቤቶችን በማጠናከር  የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ለነፍሰ ጡር እናቶች አገልግሎት የሚሰጡ 277 አምቡላንሶች  እንዳሉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም