በአገሪቱ ከ18 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት የተፋሰስ ልማት ስራዎች ተጀምረዋል

75

አዲስ አበባ  ጥር 15/2011 በተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ከ18 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራዎች መከናወን ጀምረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር የኮሙኑኬሽን ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት በዘንድሮው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ከጥር 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ የተፋሰስ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።

300 ሺህ ቀያሽ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አርሶ አደሮች ከ26 ሺህ በላይ የቅየሳ መሳሪያዎችን ለስራው ዝግጁ በማድረግ ወደ ተግባር ገብተዋል።

በዘርፉ አማራጭ የሥራ እድሎች የሚፈጠሩባቸውን አሰራሮች ለመተግበር እየተሰራ ሲሆን በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ ከ256 ሺህ በላይ ሴቶችና ወጣቶች የስራ እድል ይፈጠርላቸዋል።

የተፈጥር ሃብት ጥበቃ ስራው የአፈርን ለምነት በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

በኅብረተሰቡ በጋራ የመስራት ልምድ የተራቆቱ መሬቶችን በደን የመሸፈንና የአፈር መሸርሸርን የመከላከል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ አገሪቱ ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቷንም አውስተዋል።

ለ30 ቀናት በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች የሚሳተፉ ሲሆን የተጎዳ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ አድርጎ የመከለልና የተለያዩ የእርከን ስራዎች ይከናወናሉ።

ለዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ መመሪያ ተዘጋጅቶ በሳይንሳዊ መንገድ ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ተግባር መገባቱም ተጠቁሟል።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራን በማሳደግና የአፈርን ለምነት በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን በእጥፍ ለማሳደግ ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ተግባራትን በማከናወነ ላይ መሆኑን አቶ አለማየሁ ገልጸዋል።

ከህብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፋሰስ ልማቶች ሥነ-ህይወታዊና አካላዊ ሁኔታ ፈትሾ መንከባከብና ለእርከኖች እድሳትና ጥገና ማድረግ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም