በደቡብ ወሎ 78 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በበጋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሳተፉ ነው

62

ደሴ ጥር 15/2011 በደቡብ ወሎ ዞን 78 ሺህ  የሚጠጉ ሰዎች በተያዘው የበጋ ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሰማራታቸውን የዞኑ ሴቶች ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ አስታወቀ።

በስራው ላይ የተሰማሩት ወጣቶችና ሌሎችም የህብረሰተብ ክፍሎች  ናቸው፡፡

ከተሰማሩባቸው የስራ መስኮች መካከል ደም ልገሳ ፣ የከተማ ፅዳትና ውበት፣ የውሃ መፋሰሻ ቦዮች ጠረጋ፣ የአቅመ ደካማ ቤቶችን መስራትና መጠገን፣ የደረሱ የአርሶ አደሮችን ሰብል መሰብሰብ  ይገኙበታል።

በመምሪያው  የወጣቶች ጉዳይ ማካተት ንቅናቄ ተሳትፎ ባለሙያ አቶ ሰለሞን ተምትም ለኢዜአ እንደገለፁት ከህዳር ወር 2011ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን በተከናወነው  የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ21 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡

በዚህም  2 ሚሊዮን 700ሺህ ብር  የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ተደርጓል።

ወጣት ኢማን አሊ በደሴ ከተማ  የቀበሌ አምስት  ነዋሪ ስትሆን  በሳምንት አንድ ቀን በራሷ ተነሳሽነት በከተማ  ፅዳትና ውበት ስራ እየተሳተፈች መሆኗን ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት ተናግራለች፡፡

በምታከናውነው የበጎ አድራጎት ተግባራትም አካባቢውን በማፅዳት ተስማሚ የሰው ልጅ መኖሪያ ለመፍጠር በማገዟ የህሌና ርካታ እንደሚሰማት ገልጻለች፡፡

ሌላው  የቀበሌ ስምንት ነዋሪ ወጣት  ጀማል ሰይድ እንዳለው ጓደኞቹን በማስተባበር ማህበር መስርተው በየሶስት ወሩ ደም እየለገሱ ነው፡፡

እስካሁንም  ሁለት ጊዜ ደም መለገሱንና በከተማ ጽዳት ዘመቻም እየተሳተፈ መሆኑን ተናግሯል፡፡

በዞኑ በክረምቱ የሚከናወነውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በበጋውም ባህል ሆኖ በማስቀጠል እስከ ዓመቱ መጨረሻ 325 ሺህ ሰዉ በበጋ በጎ ፈቃድ በማሳተፍ  65 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም