በዞኑ በተመቻቸላቸው ከወለድ ነፃ ብድርና የመስሪያ ቦታ ሃብት ለማፍራት መብቃታቸውን ተጠቃሚዎች ገለጹ

55

ሰቆጣ ጥር 15/2011 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን በተመቻቸላቸው ከወለድ ነፃ ብድርና የመስሪያ ቦታ ሕይወታቸውን ለመምራትና ሃብት ለማፍራት መብቃታቸውን የተዘዋዋሪ ብድር ተጠቃሚዎች ተናገሩ፡፡

በዞኑ በአስቸጋሪ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ከ300 በላይ ሴቶች ብድር ተጠቃሚ ሆነዋል።

ተበዳሪዎቹ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት በተሰጣቸው ብድርና በመስሪያ ቦታው በመጠቀም ሕይወታቸውን በሚለውጡ ተግባራት በመሰማራት ለውጥ እያመጡ ናቸው።

ሴቶችን መሠረት ያደረገው ተዘዋዋሪ ብድር ስርጭት መመቻቸቱ ሃብት ለመፍጠር ችለናል ብለዋል።

በዝቋላ ወረዳ ጽጽቃ ከተማ ነዋሪ ወጣት አሰፉ ተክሉ በተመቻቸላት ብድርና መስሪያ ቦታ በመጠቀም በአነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ በመሰማራት ሕይወቷን እየቀየረች መሆኗን ትናገራለች።

የአሥረኛ ክፍል ትምህርቴን ካጠናቀቀች በኋላ ምንም ዓይነት ገቢ ስለላልነበራት ራሷን ማስተዳደር ተቸግራ መቆየቷንና በዚህም መኖሪያዋን ቀይራ በቤት ሠራተኛነት ተቀጥራ ለመሥራት ያቀደችበት ጊዜ እንደነበርም ገልጻለች፡፡

''ያኔ ከወለድ ነጻ በተደረገልኝ ብድርና የመሸጫ ሱቅ በመጠቀም የጀመርኩት ንግድ አሁን ላይ የተሟላ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ባለቤት ከመሆን አልፎ 35 ሺህ ብር መቆጠብ ችያለሁ'' ብላለች፡፡

በሰቆጣ ከተማ በተመቻቸላት ብድር በሻይና ቡና ንግድ የተሰማራችው ወጣት ኢየሩሳሌም ገብረ እግዚአብሔር በበኩሏ ቀደም ሲል በችግር ሕይወቷን ትመራ እንደነበር ተናግራለች።

ነገር ግን ለሴቶች የተፈቀደውን ልዩ ብድር በመጠቀም ሥራዋን አሁን ወደ ምግብ ቤት ደረጃ ማሳደጓን ገልጻለች።

በሳዑዲ ዓረቢያ ለሁለት ዓመታት አስከፊ ስደት ሕይወቷን መርታ ወደ አገሯ መመለሷን የምትናገረው ወጣት ጀሚላ ኑሩ ሐሰን በበኩሏ ባገኘችው የ10 ሺህ ብር ብድርና መስሪያ ቦታ በመጠቀም በቡናና ሻይ አፍልቶ መሸጥ ሥራ ተሰማርቻለሁ ብላለች ፡፡

''በነበርኩበት የስደት ኑሮም የሰራሁትን ገንዘብ እንኳ ሳይከፈለኝ ስቃይና በደል የተሞላበት ነበር።ከትንሽ ስራ በመነሳት ትልቅ ደረጃ መድረስ እንደሚቻል የስደት ኑሮዩ አስተምሮኛል‘’ ብላለች።

ሥራዋን ወደ ሴቶች የውበት ሳሎን ለማሳደግ ማቀዷንም አስታውቃለች፡፡

በዞኑ ሰቆጣ ከተማን ጨምሮ በዝቋላና ጋዝጊብላ ወረዳዎች ባለፉት አራት ዓመታት 311 ወጣት ሴቶች ከወለድ ነፃ የተዘዋዋሪ ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ያሉት ደግሞ የዞኑ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ መምሪያ የማደራጃ ባለሙያ አቶ በሪሁን ታመነ ናቸው፡፡

ዘንድሮ ለ101 ሴቶች በሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ማሰራጨቱን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ በአስቸጋሪ ኑሮ ለሚገኙና ሥራ እድል ለተፈጠረላቸው ሴቶች ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ብድር መሰራጨቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም