ኢትዮጵያ እና ሰርቢያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተገለጸ

108

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 ኢትዮጵያና ሰርቢያ ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ዶክተር ማርቆስ ተክሌ በኢትዮጵያ የሰርቢያ አምባሳደር አሌክሳንድራ ሪሲቲክን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለዋል።

በዚሁ ወቅት የሁለቱ አገራት ዲፕሎማቶች እንደገለጹት ሁለቱ አገሮች ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እየሰሩ መሆኑን ማሳወቃቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያና ሰርቢያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው ትብብራቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ይበልጥ ተቀራርበው እየሰሩ ነው ብለዋል።

አምባሳደር አሌክሳንድራ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን እድገት ያደነቁ ሲሆን አክለውም ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር የሰርቢያ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ እንዲሰማሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ሰርበያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1944 ዓ.ም ሲሆን ሰርቢያ ከ1947 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ኤምባሲዋን ከፍታ እየሰራች ትገኛለች።

ኢትዮጵያ ደግሞ ጣልያን ሮም በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ከሰርቢያ ጋር ያላትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደምታካሄድ ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም