“ፊላ” የተሰኘዉ የደራሼ ማህበረሰብ ባህላዊ የሙዚቃ አጨዋወቱን በዓለም በማስተዋወቅ የአገር ገጽታን መገንባት ይገባል

439

አርባምንጭ  ጥር 14/2011 “ፊላ” የተሰኘውን የደራሼ ማህበረሰብ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያና አጨዋወቱን በዓለም በማስተዋወቅ የአገር ገጽታን መገንባት እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስገነዘበ።

መሣሪያውንና የአጨዋወት ስልቱን  በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የጥናትን ምርምር ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡

መሣሪያውን ለማስተዋወቅ የተዘጋጀ ባህላዊ ፌስቲቫል ትናንት በጊዶሌ ከተማ ተካሂዷል፡፡ጥናታዊ ጽሑፍም ቀርቧል፡፡

የደራሼ ማህበረሰብ አገር በቀል ሀብት የሆነው “ፊላ” ከሸንበቆና ቀርከሃ የሚሰራ የትንፋሽ መሣሪያ ሲሆን፣በአንድ ጊዜ ከ24 እስከ 30 የሚሆኑ ሰዎች የሚጫወቱበት ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የባህል ተመራማሪ አቶ ፍሬው ተስፋዬ ባቀረቡት ጽሁፍ እንደገለጹት “ፊላ” ባህላዊ የትንፋሽ መሣሪያ በደራሼ ማህበረሰብ የተፈለሰፈ ነው ፡፡

የመሣሪያውን ድምፅ ምጣኔ ከጭፈራ ስልት ጋር በማሳመር በሕዝቦች መካከል አንድነትን በመፍጠር ዘመናት ማስቆጠሩንም ተናግረዋል፡፡

በመሣሪያው የታጀበው የሙዚቃ ስልት በዓላትን የሠርግና የደቦ ሥነ-ሥርዓትን ከማድመቅም በላይ፤ ንጉሣዊም ሆነ መንግሥታዊ እንግዶችን በክብር ለመቀበል  ይውላል ብለዋል፡፡

ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የጃዝ ሙዚቃ አባት ክቡር ዶክተር ሙላቱ አስታጥቄ ዘመናዊ የማህበረሰቡን ሙዚቃ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቃቸውንም አስታውሰዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ጃዝን ቀደም ብሎ የተጫወተው የደራሼ ማህበረሰብ ወይስ ምዕራባውያን የሚል ለክርክር ሊያስነሳ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

አርቲስት ሚካዔል ሚሊዮን ጥበቡ ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያለዉ በመሆኑ የደራሼ ብቻ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያ ሀብት በመሆኑ በዓለም አቀፍ መድረኮች ቢተዋወቅ ገጽታ ሊገነባ ይችላል ብለዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር ተወካይ አቶ ካሳሁን አያሌው በበኩላቸው መሣሪያውና የአጨዋወት ጥበቡ ማህበረሰቡን በማግባባት ለልማት የሚያነሳሳ አቅም የሚፈጥር ስለሚያመነጭ በዓለም አቀፍ መድረኮች መተዋወቅ ያለበት አገር በቀል ሀብት ነው ብለውታል፡፡

በመሆኑም ሚኒስቴሩ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኝ በምርምርና ጥናት  የታገዙ ሥራዎች  አግባብ ካላቸው የመንግሥት አካላትጋር   እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል ፡፡

መሣሪያው በሚሌኒየም አዳራሽ በተከናወነና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ በተገኙበት መድረክ  እንዲተዋወቅ መደረጉን የገለጹት የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህልና ታሪክ ዳይሬክተር አቶ መልካሙ ጋጋዶ ናቸው፡፡

በቅርቡም በዓለም አቀፍ ፊልም ሠሪዎች ባህሉ እንዲቀረጽ ፕሮግራም መያዙን አስረድተዋል።

መሣሪያው በደራሼ አካባቢ የሰው ልጅ መኖር ሲጀምር እንደተዋወቀ የተገለጸ ሲሆን፣ የድምጽ ምጣኔና የጭፈራ ስልቱ ጥልቅ መደማመጥና መናበብን ይጠይቃል ተብሎለታል፡፡

የደራሼ ወረዳ ልማት ማህበር ባዘጋጀው ፌስቲቫል የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ተወካዮችና አርቲስቶችን የሚያካትቱ ባለድርሻ አካላት ታድመዋል፡፡