ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዳቮስ ከዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አደረጉ

645

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ ካለው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ስብስባ ጎን ለጎን ከዓለም አቀፍ ተቋማት የስራ ሃላፊዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።

የ2019 የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ዛሬ በይፋ የተጀመረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጉባኤ ጎን ለጎን ከዱባይ ኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ መሀመድ አል ሼይባን ጋር መወያየታቸውን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢንቨስትመንት ፈንድ ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ በመስተንግዶና በእርሻ ቢዝነስ መዋእለ ንዋይ ለማፍሰስ ፍላጎት እንዳለውም ተገልጿል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዳቮስ ኦፕን ሶሳይቲ ፋውንዴሽን ኃላፊ ጆርጅ ሶሮስ ጋር ውይይት አካሂደዋል።

ሁለቱ ወገኖች በምርጫ፤ በዲሞክራሲያዊ ስርዓት፤ በፍትህ እና በኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እንዲሁም በተቋማዊ የቁጥጥር ማሻሻያዎችና ተግደሮቶቻቸው ዙሪያ ሀሳቦብ መለዋወጣቸው ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።

የሲቪል ማህበራትን በማስፋፋት እና በተሻሻለ የስደተኞች ህግ ላይ በማተኮር ኢትዮጵያ ያሳየችውን እመርታ ጆርጅ ሶሮስ ማድነቃቸውም ተጠቅሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በስዊዘርላንድ ዳቮስ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ኢትዮጵያ ባለፉት አስር ወራት ስላስመዘገበቻቸው ለውጦች ንግግር እንዲያደርጉ ይጠበቃል።

በሌላ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከዳቮሱ የኢኮኖሚ ፎረም ጎን ለጎን ከስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲሲ ጋር በሁለትዮሽና በባለብዙ መድረኮች በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ዶክተር ወርቅነህ የሁለቱን አገሮች ዲፕማሲያዊ ግንኙነት አድንቀው በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ስላለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲሱ አመራር እየተካሄደ ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በአገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማምጣት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና የሰብዊ መብት ለማስከበር እንዲሁም የሚዲያ ነጻነትን ለማስጠበቅ ዓይነተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የተለያዩ በርካታ አዋጆችም በመጠናትና በመሻሻል ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የስዊዘርላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲሲ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ እድንቀው፣ የስዊዘርላንድ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚ ትብብር እንዲያጠናክሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከዚህ በፊት በሁለቱ አገሮች መካከል የተደጋጋሚ ቀረጥን ለማስቀረት እንዲቻል የተጀመረው ስምምነት ተጠናቆ ወደ ተግባር እንዲገባ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እንደሚጥሩም ተስማምተዋል።

በተጨማሪም በሁለቱ አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታዎች ደረጃ የተጀመረው የፖለቲካ ምክክር ወቅቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ እና በስዊዘርላንድ መካከል የመጨረሻውና 3ኛው የፖለቲካ ምክክር መድረክ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም በበርን ስዊዘርላንድ መካሄዱ ይታወቃል።

ስዊዘርላንድ በኢትዮጵያ በፌዴራሊዝም ስርዓት ግንባታና በመልካም አስተዳዳር ዘርፎች የሚደረጉ ስራዎችን በመደገፍ ላይ እንደምትገኝ ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።