የገቢ ለልማት ኮንፍረንስ በመቀሌ ተካሄደ

394

መቀሌ  ጥር 14/2011 ” ግዴታየን እየተወጣሁ መብቴን እጠይቃለሁ ” በሚል መሪ ሀሳብ የገቢ ለልማት ኮንፍረንስ ዛሬ  በመቀሌ ከተማ  ተካሄደ፡፡

በከተማው የሰማእታት ሀወልት አዳራሽ በተካሄደው ኮንፍረንስ ወቅት የተገኙት  የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ እንደገለጹት ሀገሪቱ ከግብር ማግኘት የሚገባትን እያጣች ነው፡፡

በሁለተኛ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመን የግብር አሰባሰብ ምጣኔው ከ17 በመቶ በላይ ለማድረስ ቢሆንም የእስካሁን አፈጻጸም ዝቅተኛ  መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

የግብር ሰብሳቢው ሴክተርና ግብር ከፋዮች  ግዴታቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ለዚህ በምክንያትነት ከጠቀሷቸው መካከል ይገኙበታል፡፡ 

ሚኒስትር ዴኤታው  ” አካሄዳችን በመፈተሽ  ማስተካከል ይኖርብናል “ብለዋል፡፡

በኢንቨስትመንትና በንግድ ስራ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ግብር በመክፈል ለሀገሪቱ እድገትና የመሰረተ ልማት ግንባታ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የገቢ ሰብሰቢ ሴክተሩም እንዲሁ፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አብራሀም ተከስተ በበኩላቸው ” የመንግስት ህግና ስርዓት የማይከተሉ ነጋዴዎች  ላይ  እርምጃ መውሰድ እንጀምራለን ” ብሏል።

ለዚህም ደግሞ  የህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡

በኮንፈረንሱ ከተሳተፉ የንግድ ማህበረሰብ አባላት መካከል በመቀሌ በምግብ ዝግጅት የተሰማሩት  ወይዘሮ ብርሃን ኃይሉ ከማገኘው ገቢ በአግባቡ ግብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ለመንግስት ገቢ ያደረጉትን 150ሺህ ብር  በማሳየነት ጠቅሰዋል፡፡

” ግብር የማይከፍሉ የንግድ ማህበረሰብ  ጉዳቱ ለልጆቻቸውና ቀጣዩ ትውልድ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል “ብለዋል፡፡

ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታ  መሆኑን በመገንዘብ ባለፈው ዓመት  45ሺህ ብር  ገቢ ማድረጋቸውን የተናገሩት ደግሞ በዓዲግራት ከተማ ዳቦ በማከፋፈል ስራ የተሰማሩት  አቶ ሃድጉ ተስፋዬ ናቸው።

” ግብር የማይከፍሉ ነጋዴዎች ግን እየጎዱን ስለሆነ መንግስት ሊያስታግስልን ይገባል” ብለዋል፡፡

ለአንድ ቀን በተካሄደው ኮንፍረንስ ከክልሉ  12  ከተሞች የተውጣጡ 700 የሚሆኑ የንግድ ማህበረሰብ የተሳተፉ ሲሆን   በንግድ ፍቃድ አሰጣጥና ስረዛ ፣ በግብር አሰባሰብ የሚታዩ አዎንታዊና አሉታዊ እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡