የአድዋ የእግር ተጓዦች ለፍቅር፣አንድነትና ሰላም መጎልበት ሚናቸውን እየተጫወቱ መሆኑን አስተዳደሩ ገለጸ

48

ደሴ ጥር 14/2011 የአድዋ የእግር ተጓዦች የአባቶችን ታሪክ በመዘከር በሕዝቦች መካከል ለፍቅር፣አንድነትና ሰላም እንዲጎለብት ሚናቸውን እየተጫወቱ መሆኑን የደሴ ከተማ አስተዳደር ገለጸ።

ስድስተኛው ዙር ጉዞ የአድዋ የእግር ተጓዦች ደሴ ከተማ ዛሬ ሲገቡ በከተማዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የአስተዳደሩ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ማህደር አራጌ በአቀባበሉ ወቅት እንደተናገሩት የጥንት አባቶቻችንን ታሪክ በማስታወስ በሕዝቦቿ መካከል ፍቅር፣አንድነትና ሰላም እንዲሰፈን እገዛ እያደረጉ ነው።

ተጓዦቹ ታሪክን ከማስታወስ ባሻገር፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት እንደሚያስችሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ሳይሸረሸር ተባብሮ ለመሥራት ትምህርት እንደሚቀሰምበትም ኃላፊው እምነታቸውን ገልጸዋል።

ከተጓዦች መካከል ወጣት ባርክልኝ ወልደ ዮሐንስ የአባቶችን ታሪክ ለማስታወስ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን ለማስቀጠል፣ የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶችን ለማጎልበት በጉዞው መሳተፉን ተናግሯል፡፡

በዓሉን በእግር ተጉዘው ለማክበር ከአዲስ አበባ የተነሱት 14 አባላት ቢሆኑም፤ በየደረሱባቸው ከተሞች ወጣቶች እየተቀላቀሏቸው ዛሬ ቁጥራቸው 22 መድረሱንም አስታውቋል፡፡

በየከተሞቹ ከጠበቁት በላይ ለሆነው አቀባበልና ድጋፍ  ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

አባቶችን ዘርና ሃይማኖት ሳይበግራቸው ዳር ድንበሯን ጠብቀዉ ያቆይዋትን አገር ለትውልድ ለማስተላለፍ ታሪክን ማወቅ ያስፈልጋል ያለው ደግሞ ከደሴ ከተማ የእግር ጉዞውን የተቀላቀለው ወጣት ሚካኤል ዳንኤል ነው።

በጉዞው የአገሩንና የሕዝቦቿን ባህልና ታሪክ በመረዳት በዓሉን ታሪክ በተሰራበት በአካል ለማክበር መነሳቱን ተናግሯል፡፡

ተጓዦቹ በቀን እስከ 50 ኪሎ ሜትር በመጓዝ የካቲት 23 ቀን 2011 አድዋ ከተማ እንደሚገቡ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጉዞውን የሚያስተባብረው የአድዋ በጎ አድራጎት ማህበር አፄ ምኒልክንና የድል ሠራዊታቸውን የሚያስታውስ ሐውልት በወረኢሉ ከተማ ለመገንባት ሰሞኑን የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡

የቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ወደ ውጫሌ ከዚያም ወደ መርሳ ይሆናል።

ኢትዮጵያውያን የጣልያን ወራሪ ኃይል አድዋ ላይ ካሸነፉ ዘንድሮ 123 ዓመት ይሞላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም