ስንዴን በኩታ ገጠም ያለሙ አርሶ አደሮች በሄክታር እስከ 80 ኩንታል ምርት አገኙ

908

ጎባ ጥር 14/2011 የዳቦ ስንዴን በኩታ ገጠም መሬት በማልማት  በአንድ ሄክታር መሬት  እስከ 80 ኩንታል ምርት መሰብሰብ እንደቻሉ በባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

በዞኑ በመኸሩ ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘር ከለማው 359 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው ምርት መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡

አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ እንደገለፁት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችንና  ምርጥ ዘር መጠቀማቸው ውጤታማ  አድርጓቸዋል፡፡

አቶ አለሙ ከበደ በጊኒር ወረዳ አርዳ የቀብሶ ቀበሌ አርሶ አደር ሲሆኑ ኩታ ገጠም ማሳ ካላቸው ሌሎች 24  አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት”ቀቀባ” የተባለ የስንዴ ምርጥ ዘር ማልማታቸውን በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል፡፡

በመስመር የመዝራትና ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረጋቸው በሄክታር 80 ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መብቃታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኩታ ገጠም የማልማቱ ልምድ የተሻሻሉ አሰራሮች ለመጠቀምና ገበያንም በተደራጀ አግባብ ለመፈለግ እንደሚያግዝ የጠቆሙት አርሶ አደሩ ተጠቃሚነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር መንግስት የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር ግርማ ደምሴ በበኩላቸው ከዚህ በፊት ከተለምዶ የግብርና አሰራር  በሄክታር ማሳ ላይ ከ20 ኩንታል በላይ ምርት አግኝተው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡

“በተለያዩ ጊዜያት በተሰጠን ስልጠናና የባለሙያ ድጋፍ የአመራረት ዘይቤያችን በመቀየር ምርታማነታችንም ከሁለት እጥፍ በላይ በማሳደግ 51 ኩንታል ስንዴ ማምረት ችያለሁ”ብለዋል፡፡

መንግስት አርሶ አደሩ በብዙ ልፋት ከሚያመርተው ምርት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን በአካባቢያቸው  የስንዴ ምርታቸውን  በግብዓትነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች የሚገነቡበት ምቹ ሁኔታ ቢያመቻች እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።

የወረዳው የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልቃዲር አደም በወረዳው በመኽሩ ወቅት በስንዴ ሰብል ከለማው 90 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ  40 በመቶ የሚሆነው በኩታ ገጠም አሰራር የለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች የመጠቀም ልምድ እየዳበረ መምጣቱን የጠቀሱት ኃላፊው በወረዳው በኩታ ገጠም ማሳ ያለሙ አርሶ አደሮች ከ55 እስከ 80 ኩንታል የሚደርስ ምርት መሰብሰባቸውን አመልክተዋል፡፡

ጊኒር ጨምሮ በባሌ የተለያዩ ወረዳዎች በመኸሩ ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘር  ከለማው 359 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነው መሰብሰቡን ያስታወቁት ደግሞ በዞኑ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አለምእሸት አለማየሁ ናቸው፡፡

ቀሪውን ደግሞ  እንደወረዳዎቹ የስነ – ምህዳር ሁኔታ ሳይባክን  ለመሰብሰብ እየተሰራ ነው ፡፡

አስተባባሪው እንዳሉት በዞኑ በኩታ ገጠም አሰራር ከ162 ሺህ የሚበልጥ መሬት በስንዴ ሰብል እንዲለማ ተደርጓል ።

አርሶ አደሩ በመስመር የመዝራትን ጨምሮ ሌሎች ምርጥ ዘርና የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን የመጠቀም ዝንባሌው እያደገ በመምጣቱ ምርታማነቱም እንዲሁ ሊጨምር መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በተወሰኑ አርሶ አደሮች ዘንድ እየታየ ያለውን

የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች አጠቃቀም ምርጥ ተሞክሮ ወደ ሌሎች አርሶ አደሮች ለማስፋት ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፡፡

ከገበያ ትስስር ጋር ተያይዞ አርሶ አደሮቹ የሚያነሱትን ችግር ለመፍታት በሀገር ውስጥ ስንዴን በግብዓትነት ከሚጠቀሙ  የዱቄትና የምግብ ማቀነባበሪያ  ፋብሪካዎች ጋር በቅርቡ ስምምነት መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡

በባሌ ዞን በ2010/2011 የምርት ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘር  ከለማው 359 ሺህ ሄክታር መሬት ስምንት ሚሊዮን 500ሺህ  ኩንታል ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት  ፕሬዝደንት አቶ ለማ መገርሳ  በቅርቡ  በባሌ ዞን ስንዴን በኩታ ገጠም አሰራር ዘዴ ያለሙ አርሶ አደሮች ማሳ በስፍራው በመገኘት መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡