ሰላማችንን ለመጠበቅ ሁላችንም ድርብ ኃላፊነት አለብን- የቀድሞ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ

96

አዲስ አበባ ጥር 14/2011 ከምንም በላይ ዋጋ ያለውን ሰላማችንን ለመጠበቅ ሁላችንም ድርብ ኃላፊነት አለብን ሲሉ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ጉባዔ ሰብሳቢ የቀድሞ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ተናገሩ።

በኦነግና ኦዴፓ መካከል በተፈጠረው ችግር ላይ የሚመክር ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ይህ ምክክር በኦሮሞ አባገዳዎች ጉባዔ የተዘጋጀ ሲሆን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ አመራሮችን ጨምሮ አባገዳዎች፣ እናቶች፣ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን ተሳትፈውበታል።

መድረኩን በምርቃት ከፍተው ንግግር ያደረጉት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ጉባዔ አባገዳ በየነ ባሰሙት መልእክት አሁን የገጠመንን ችግር ለመፍታት ትናንት የነበርንበትን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው ብለዋል።

"ለእኛ ሰላማችን ቤታችን ነው" ያሉት አባገዳ በየነ፤ ከሰላም ውጭ ደጅም ቤትም ስለሌለን "እናንተ እርቅ እስካላወረዳችሁ ድረስ ወደ ቤት አንገባም" በማለትም በአጽንኦት አሳስበዋል።

አባ ጨፌ ጫላ ሶሪ በበኩላቸው እርቅ ለማውረድ ከልብ መምከርና ለውሳኔ ቁርጠኛ መሆን ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ ፓርቲዎችም ይህንኑ ተረድተው ወደ እርቅና መግባባት መምጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

በአሁኑ ወቅትም ምክክር እየተካሄደ ሲሆን ከሁለቱም ፓርቲዎች የችግሮቹና አለመግባባቶቹ መነሻና ያስተከተለውን ጉዳት የተመለከተ ማብራሪያ እየተሰጠ ነው።

በመድረኩ መክፈቻ ላይ አባ ገዳዎችና እናቶች ሲንቄ ይዘው የሰላም ጥሪ ስነ ስርዓት አከናውነዋል።

በመቀጠልም በጉዳዩ ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጎ ከውሳኔ እንደሚደረስ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም