የህንድ የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እየተሳቡ ነው

61

ጥር 14/2011 የህንድ የጨርቃጨርቅ ማምረቻ ኩባንያዎች በኢትዮዽያ በተፈጠረው ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ በመሳብ በባንግላዴሽና በካምቦዲያ ያሏቸውን ፋብሪካዎች በማንሳት ወደ ኢትዮዽያ እያመሩ መሆናቸውን ቢዝነስ ስታንዳርድ ዘግቧል።

ኬፒአር ሚል የተሰኘው ግዙፉ የህንድ የጨርቃጨርቅ አምራች በኢትዮዽያ ፋብሪካውን በመትከል ሰፊ የሰው ሃይል፣ ከቀረጥ ነፃና ወደ ዩኤስ አሜሪካና አውሮፓ ገበያ ቅርብ የሆነውን የመርከብ አገልግሎት ለመጠቀም መወሰኑን ገልጿል።

ኬፒአር የተሰኘው የጨርቃጨርቅ ኩባንያ በሃገሪቱ ከሚንቀሳቀሱት ሬይሞንድ፣ አርቪንድ ፣ ቤስት ኮርፖሬሽንና ጄጄ ሚልስ ከተሰኙት ፋብሪካዎች ጋር በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር የጨርቃጨርቅ ሱቆችን በመገንባት ወደ ስራ ለመግባት በመንደርደር ላይ ይገኛል።

ኬፒአር 5 ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ በማድረግ አንድ ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር አስር ሚሊዮን የምርት አይነቶችን ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን እንዲሁም በኢትዮጵያ ብቻ 2 ሚሊዮን ጃኬቶችን የማምረት አቅምን ያዳበረው ሬይሞንድስ ፣ ቤስት ኮርፖሬሽን፣ ኤስሲኤም፣ አርቪንድና ጄጄ ሚልስ ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ ፋብሪካዎቻቸውን ከከፈቱት የአልባሳትና ጨርቃጨርቅ ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ መንግስት ከፈጠረው የኢንቨስትመንት ዕድል በተጨማሪ በህንድ የአንድ ሰራተኛ ደሞዝ በወር ከ130 እስከ 150 ዶላር ሲሆን በኢትዮዽያ ግን ከ60 ዶላር እንደማይበልጥ የኩባንያው ተወካይ ገልፀው በሃገሪቱ የኤሌክትሪክ ሃይልን በ3 የአሜሪካን ሳንቲም ማግኘት የሚቻል ሲሆን በህንድ ግን የሃይል አቅርቦቱ ዋጋ ከ10 እስከ 12 የአሜሪካን ሳንቲም እንደሆነም አክለዋል።

ሰፊ የሰው ጉልበት፣ የሃይል አቅርቦት ፣ ወሳኝ የገበያ አማራጮች እንዲሁም ግልፅ የሆነ የታክስ ህጎች ኩባንያዎቹን ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር እንደሳባቸው ቢዝነስ ስታንዳርድ አክሎ አስረድቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም