በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ተሳትፏል

66
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሰባት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ100 በላይ በሚሆኑ ከተሞች በተካሄደው ተመሳሳይ የሩጫ ውድድር ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ መሳተፉ ተገልጿል። በአዲስ አበባ በተካሄደው ውድድር ከ90 ሺህ በላይ ህዝብ ተሳትፏል። "ስለ ዓባይ እሮጣለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደውን የሩጫ ውድድር በመተባበር ያዘጋጁት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ናቸው። ከገቢ ማሰባሰብ ባሻገር ህዝቡ ለግድቡ ግንባታ ሂደት ተጨማሪ ንቅናቄ በመፍጠር ጉዳዩ የዘውትር አጀንዳው እንዲሆን ማድረግ የስፖርታዊ ውደድሩ ዓላማ ነው ተብሏል። የሩጫ ውድድሩን በይፋ ያሰጀመሩት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሥራ ኃላፊዎች፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞችና ሌሎች እንግዶች ናቸው። በዚሁ ወቅትም "አሻራዬን አኑሬአለሁ!" የሚል መልዕክት የታተመበትና የህዳሴ ግድብ ምስል ያረፈበት የደረት ፒን ሽያጭ በይፋ ተጀምሯል። ከመስቀል አደባባይ የተጀመረው ውድድሩ በሜክሲኮ ቡናና ሻይ፣ በገነት ሆቴል ቄራ - ከቄራ መገንጠያ በጎተራ ማሳላጫ አድርጎ መድረሻውን መስቀል አደባባይ አድርጎ ተጠናቋል። በውጤቱም በሴቶች ዓለም ገብረእግዚአብሔር፣ በላይነሽ ገብረሀናና ሙሉሰው ሰውነት፤ በወንዶች ደግሞ ዮናስ ለታ፣ ስንታየሁ ደርቤና መርከቡ ወዳጄ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ደረጃ በመያዝ ውድድሩን አጠናቀዋል። በአካል ጉዳተኞች የዊልቸር ውድድር የተሳተፉት ደባስ አበራና በሪሁን ይታገስ በቅደም ተከተል አንደኛና ሁለተኛ ሆነዋል። በሁለቱም ጾታዎች ከአንድ እስከ ሶስትና በአካል ጉዳተኞች የዊልቸር ውድድር አንደኛና ሁለተኛ ለወጡት ተሳታፊዎች የሜዳሊያ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። በሁለቱም ጾታዎች ከአራት እስከ 20 ለወጡ የሩጫው ተሳታፊዎች ደግሞ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ርስቱ ይርዳ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ለአሸናፊዎች ሽልማቱን አበርክተዋል። ለሩጫው ከተዘጋጀው 250 ሺህ ካኔቴራ ሽያጭ 25 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡም ተጠቁሟል። የዘንድሮው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሩጫ ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደ ሲሆን ከዚህ በፊት በ2005 እና በ2009 ዓ.ም በተካሄዱ ተመሳሳይ ሁለት ውድድሮች በአጠቃላይ ከ760 ሺህ በላይ ሰዎች መሳተፋቸው ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም