ውህደት ለመፍጠር በሂደት ላይ የሚገኙት ስምንቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዜጋ ፖለቲካን እንደሚያቀነቅኑ ተገለጸ

537

አዲስ አበባ  ጥር 13/2011 ውህደት ለመፍጠር በሂደት ላይ የሚገኙት ስምንቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሰርቱት ፓርቲ የዜጋ ፖለቲካን የሚያቀነቅን ይሆናል ተባለ።     

የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲን፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤትንና ብሩኀ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን ጨምሮ ስምንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የሚገኙት በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተበታትነው ለየቅል ከመንቀሳቀስ ይልቅ ወደ ሦስት እና አራት ቢሰባሰቡ ለአገራቸውና ህዝባቸው የተሻለ ተግባር በመፈፀም ለውጤት እንደሚበቁ መክረው ነበር። 

ፓርቲዎቹ ይህንን የሚያደርጉ ከሆነም መንግሥት አስፈላጊውን የኃብትና የሀሳብ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ማረጋገጫ መስጠታቸውም የሚታወስ ነው።

ይህን ተከትሎም የተለያዩ ፓርቲዎች ውህደት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀምረዋል።        

ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት፣ ብሩኀ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ቱሳ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ዲሞክራሲያ ድርጅት፣ ኢትዮጵያችን ህዝባዊ ንቅናቄ፣ የኦሞ ህዝቦች ዲሞክራሲያዊ ህብረትና የደቡብ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ይጠቀሳሉ።

ከስምንቱ እነዚህ ፓርቲዎች መካከል ስድስቱ ከውጭ አገር የመጡ ናቸው።

ፓርቲዎቹ ውህደቱን እውን ማድረግ ይቻላቸው ዘንድም ነው ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ውይይት ያካሄዱት።  

የውህደቱ አመቻች ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ስለሺህ ጥላሁን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ውህደቱን እውን ለማድረግ ከፓርቲዎች ጋር ጥልቅ ውይይት ተደርጓል።  

በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት የማይደራደር ፓርቲ ለመፍጠር እቅድ መኖሩን የጠቀሱት አቶ ስለሺ ከውህደቱ በኋላ የሚመሰረተው ፓርቲ ዜጋን መሰረት ያደረገ ፖለቲካ ላይ የሚያተኩር እንዲሆን ሀሳብ መኖሩን አስረድተዋል።      

እንደ አቶ  ስለሺ ገለጻ የሚዋሀዱ ፓርቲዎች በሚያግባባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ መፈረሙንና  የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳዳሪያ ደንብም በረቂቅ ደረጃ መዘጋጀቱን ነው አስተባባሪው ያብራሩት።          

አቶ ስለሺህ እንደሚሉት የተዘገጃውን የመጨረሻ ረቂቅ ለውህደት አመቻችና አስተባባሪ ኮሚቴ ተልኮ በድጋሚ ለፓርቲዎች እንዲደርስ ይደረጋል። 

አስተባባሪው አክለውም በአገሪቷ የፖለቲካ ምህዳር ሰላማዊ ተሳትፎ ማድረግ ቁፍል ጉዳይ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ውህደቱ ተሳክቶ ፓርቲ ሲመሰረት ለሰላምና ለአንድነት የሚተጋ እንደሚሆን ጠቁመዋል።   

”በፖለቲካው መስክ በቀጣይ በስኬት ለመጓዝ ከተፈለገ ሁሉንም የሚያሳትፍ ተግባር ማከናወን ይገባል፤” ያሉት አስተባባሪው በፖለቲካ ድርጅቶች፣ ምሁራን በመብት ተማጓቾች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የእምነት መሪዎችን ያሳተፈ ብሄራዊ መግባባት ተግባርም ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለይ በውጭ ያሉና የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን የጥምር ዜግነት ፖለቲካ ተሳትፎ መከልከሉ ችግር መሆኑንም ይገልጻሉ።

ከሚወሃዱት ፓርቲዎች መካከል የሆነው የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ በበኩላቸው “ፓርቲያቸው ለህዝብ ጥቅም ሲባል መስዋዕትነት መክፈል ካስፈለገ እናድርገው” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ባለፈው ታህሳስ ወር 2011 ዓም ሰማያዊ ፓርቲ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ፣ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) እንዲሁም አቶ አንዱዓለም አራጌና አቶ ግርማ ሰይፉን ጨምሮ ከቀድሞ የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ አባላት ጋር ውህደት ለመፍጠር ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።

በኢትዮጵያ በተለያየ መንገድ ተደራጅተውና እውቅና ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ ከ70 የሚልቁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዳሉ ይነገራል።