በከተማዋ የመንግሰት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጀመረው ልኬትና ምዝገባ በሚጠበቀው ልክ አልተሰራም

75

አዲስ አበባ  ጥር 13/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሰት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጀመረው የቦታ ልኬትና ምዝገባ በሚጠበቀው መጠን አለመሰራቱን የከተማው ቤቶች አሰተዳደር ኤጀንሲ ገለጸ።

የከተማዋ ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን እንዲጠቁሙ በተደረገው ጥሪ መሰረት ባለፉት ጥቂት ወራት በህገ-ወጥ  መንገድ በማይገባቸው ሰዎች እጅ የነበሩ በርካታ ቤቶች ተገኝተዋል፤ የከፋ ችግር ላለባቸው የመዲናዋ ነዋሪዎችም እንዲተላለፉ ተደርጓል። 

ይሁን እንጂ ልኬትና ምዝገባው እንዲካሄድ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ባለመሰራቱ በተጀመረው እንቅስቃሴ ላይ መጓተት እንዳጋጠመው ተገልጿል።

በአጠቃለይ ካሉት 153 ሺህ 755 የመኖሪያና የንግድ ቤቶች መካከል እስካሁን በአስሩም ክፍለ ከተሞች ልኬትና ምዝገባ የተካሄደባቸው 7 ሺህ 256 ብቻ እንደሆነ በሰኔ ወር 2010ዓ.ም የተገኘው መረጃ ያረጋግጣል።

ኤጀንሲው ይሄንኑ መጓተት ያጋጠመውን እንቀስቃሴ ለማፋጠንና የይዞታ ማረጋገጫውን ለመስጠት ስራዎቹን በዘመቻ መልክ ለመስራት ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት መግባባት ላይ መድረሱን ገልጿል።

በመሆኑም  የዘመቻ ስራው በሁሉም ክፍለ ከተሞች እንዲጀመርና  የመንግሰት ቤቶች ቆጠራና ምዝገባ እንዲሁም የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን እስከ ሰኔ 2011ዓ.ም ለማጠናቀቅ ስምምነት ላይ መደረሱን ከኤጀንሲው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አመላክቷል።

የምዝገባና የይዞታ ማረጋገጫ የመስጠት ስራዎችን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የይዞታ አስተዳደርና የሽግግር ጊዜ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት በፓርሴል ልኬት ካርታውን የማዘጋጀት ስራ ይሰራል ተብሏል።

የከተማ አስተዳደሩና የመሬት ይዞታ ምዝገባ ኤጀንሲም  እያንዳንዱ የመንግስት ቤቶች እንዲመዘገቡ በማድረግ ዘመቻው የራሳቸውን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባቸውም በተደረገው ውይይት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም