የዋጋ ጭማሪ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

1080

ሀዋሳ ጥር 13/2011 በሃዋሳ ከተማ በተለያዩ የግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።

በተደራጀ መልኩ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ተገቢ አለመሆኑንና ይህን ለመቆጣጠር የሚያስችል ግብረ ኃይል መቋቋሙን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታውቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት በግብርና ምርቶችና በዳቦ ዱቄት ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል።

በአሁኑ ወቅት አዲስ የግብርና ምርት ወደ ገበያ እየገባ ቢሆንም የዋጋ ጭማሪ እንጂ ቅናሽ አለመኖሩን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

በሃዋሳ ከተማ በዳቦ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ካሚል ጉተማ እንዳሉት በግብርና ምርቶች ላይ እየተስተዋለ ያለው የዋጋ ጭማሪ ከአቅም በላይ እየሆነ መጥቷል።

“ሁልጊዜ የገበያ ዋጋ እየጨመረ ነው ያለው፤ ዛሬ ገዝተህ ነገ ከነገወዲያ ወደ ገበያ ብትሄድ የዋጋ ጭማሪ እንጂ ቅናሽ አይታይም” ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል።

“ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ መነን ገብረመድህን በሃዋሳ ከተማ ሁሉም ነገር ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አላየሁም” ብለዋል።

በከፍተኛ መጠን ተመርቷል የሚባለው ሽንኩርትን ጨምሮ በእህልና በተለያዩ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።

ወይዘሮ መነን እንዳሉት የሕብረት ሥራ ማህበራት የፍጆታ እቃዎችን ከመንግስት ተረክበው በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ በኩል ጥሩ ሥራ እየሰሩ ቢሆንም እህልና ሌሎች ሸቀጦችን በማቅረብ በኩል ክፍተት አለባቸው።

መንግስት ይህን ጉዳይ በትኩረት ተረድቶ አማራጭ መፍትሄ እንዲፈልግላቸውም ጠይቀዋል።

ምርቱን የሚያቀርቡልን ነገዴዎችና አምራቹ አርሶአደር ዋጋ በመጨመራቸው ምክንያት የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የሚናገረው ደግሞ በሃዋሳ ከተማ በእህል ንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ወጣት በላይ አየለ ነው።

ከእነዚህ በተጨማሪ በንግድ ሥራው ላይ ዋጋ እንዲጨምር የሚያደርግ ሦስተኛ አካል መኖሩንም ተናግሯል።

ሌላው በእህል ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አለማየሁ በየነ በበኩላቸው የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አምነው ጭማሪው ከምርት አቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወጤ ቶሼ በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ሃዋሰ ከተማን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ከንግድ ሥራ ጋር በተያያዘ ችግሮች እየተስተዋሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በግብርና ምርቶች ላይ የሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ከከተማ ከተማ የተለያየ ቢሆንም የነጻ ገበያ መርህን በመጣስ ከእዚህ በተቃራኒ በተደራጀ መንገድ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ቁጥጥርና ክትትል የሚያደርግ ግብረኃይል ከክልል እስከ ቀበሌ ባሉ መዋቅሮች ተቋቁሞ ወደሥራ መገባቱን ገልጸዋል።

ግብረኃይሉ የፍትህ አካላት፣ የሴት አደረጃጀቶችንና የሕብረት ሥራ ማህበራትን ባካተተ መልኩ የተደራጀ መሆኑንም ገልጸዋል።

አቶ ወጤ እንዳሉት ግብረኃይሉ ከምርት ማከማቸት፣ መሸሸግና ተገቢ ባልሆነ መልኩ ከሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ ይገኛል።

ሕብረተሰቡ ከእዚህ ጋር በተያያዘ ጥርጣሬ ሲኖረው በአቅራቢያው ባለ የንግድና ኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት በመቅረብ ማሳወቅ እንደሚችል አቶ ወጤ አስታውቀዋል።