የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች በአግባቡ ባለመቅረባቸው ለአደጋ እየተጋለጥን ነው-ሰራተኞች

64

አዲስ አበባ ጥር 13/2011የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያዎች በአግባቡ ባለመቅረባቸው ምክንያት ለአደጋ እየተጋለጥን ነዉ ሲሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጅን ሰራተኞች ተናገሩ፡፡

ደርብ ደምሰው በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰሜን አዲስ አበባ ሪጅን በቀን ሰራተኝነት ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ ከስድስት ዓመት በላይ ሆኖታል።

ከዕለታት በአንዱ ቀን የከፍተኛ መስመር ዝርጋታ ስራ እየሰራ ድንገት ኃይል ይለቀቅና ምሰሶ ላይ እንዳለ የቃጠሎ አደጋ ይደርስበታል፡፡

በጊዜው ራሱን ስቶ ከአምስት ቀን በኋላ እንደነቃ እንዲሁም ለስምንት ወር በህክምና መቆየቱን ይናገራል።  

ሌሎች የተቋሙ ሰራተኞችም በቃጠሎ አደጋዎች ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

የደህንነት መሳሪዎቹ በዕቃ ግምጃ ቤት ተከማችተዉ ቢኖሩም "እናንተ ቋሚ ሰራተኞች አይደላችሁም" በሚል ምክንያት  አይሰጡንም፣ ስራዉን ግን እንድንሰራ እንገደዳለን፤ "በዚህ ደግሞ ከቀላል እስከ ከባድ ጉዳት እንድንጋለጥ እያደረገን ነው" ሲሉ ቅሬታቸዉን አቅርበዋል።

ከሰራተኞቹ መካከል አቶ አለምነው አወቀሴፍቲ አይሟላልንም ፣ አይሰጥም ለቋሚ ሰራተኛ ሲሰጥ ለእኛ ሴፍቲ የሚባል አይሰጠንም ፒንሳ ራሱ ከሚሰጠን ላይ ነዉ የምንገዛዉ አልባሳት ከዚያችዉ ከምናገኛት ደሞዝ ላይ ነዉ የምንገዛው ሌላ ምንም የሚሟላልን ነገር የለም  ብሏል።

ሌላው ሰራተኛ ባጫ በቀለ ደግሞ ሴፍቲ  ስቶር ላይ እንደሚኖር እናያለን ሴፍቲ ስጡን ጥንቃቄ እያደረግን እንሰራለን ሄልሜት ስጡን ጫማ ስጡን ስንላቸዉ እናንተን አይመለከታችሁም እናንተ የቀን ሰራተኛ ናችሁ እንጂ ልብስ ለእናንተ አይደለም ለቋሚ ሰራተኛ ነዉ  ብለው ይመልሱልናል፡፡

የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ ስራው በባህሪው የደህንነት መሳሪያ የሚያስፈልገው ቢሆንም የደህንነት መሳሪያው ግምጃ ቤት ተቀምጦ ሰራተኛ ለአደጋ የሚጋለጥበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፤ ከግምጃ ቤት ባለመኖሩ ነው ይላል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ በበኩላቸው

ከደህንነት መሳሪዎች  ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታ  ትክክል አይደለም  ንብረት ክፍል ኖሮ ለእኛ ሰራተኛ የማንሰጥበት ምክንያት አይኖርም አንዳንዴ እየቀረበለትም የማይጠቀም ሰራተኛ አለ ይኼ የመጣዉ ከግንዛቤ ዕጥረት ነዉ።

ከቀላል እስከ ከፍተኛ መስመር ዝርጋታ ስራ እንሰራለን የሚሉት ሰረተኞቹ ተቋሙ የስራዉን ለአደጋ አጋላጭነት አይቶ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ሊያሟላልን ሲገባ ተግባሩ ግን የተገላቢጦሽ ከመሆኑም በላይ ለሚደርስብን የስራ ጉዳት ተመጣጣኝ የሆነ የደም ዋጋ እና የካሳ ክፍያም አይፈጸምልንም ይላሉ።   

ደርብ ደምሰው በበኩሉ ትራንሰፎርመር ላይ ስሰራ በተለቀቀብኝ ሀይል ተቃጥዬ  ስምንት ወር ህክምና ላይ ነበርኩኝ እግዚአብሔር ይመስገን አሁን ድኜ ወጥቼ እየሰራሁ ነው። ኢንሹራንስ ግን በአግባቡ ሊሰጡኝ አልቻሉም የሚገባኝ ነገር አልተሰጠኝም ሲል ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አንዳንድ ሰራተኞች የደህንነት መጠበቂያ መሳሪያ ቀርቦላቸውም በአግባቡ አይጠቀሙበትም  የሚል ቅሬታም ያነሳል።

ለሚደርስባቸው የስራ ላይ አደጋም ቢሆን አስፈላጊው ካሳ እና የደም ዋጋም የሀገሪቱ ህግ እና ደንብ በሚፈቅደው መሰረት ተግባራዊ ይደረጋል ተቋሙ ሰራተኞችን የመጉዳት ፍላጎት የለውም ሲሉም ይናገራሉ።

ተቋሙ ይህን ይበል እንጂ ሰራተኞቹ  "ጥያቄችንን በተደጋጋሚ ብናቀርብም  የሚሰማን አካል አላገኘንም አሁንም ቢሆን ስራውን የምንሰራው የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብን ነው፤ ህይወታችንን መስዋዕት እያደረግን ያለነውና የሚመለከተው ይየን" ሲሉ ጠይቀዋል።   

ለሀገር ኢኮኖሚ ልማት ወሳኝ በሆነው ኤሌክትሪክ ስራ ላይ ተሰማርቶ አካሉን እየጎዳና ህይወቱን መስዋዕት እያደረገ ያለው ሰራተኛ ለደህንነቱ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ።   

አሰሪ ድርጅቱም እንደየ ስራው ባህሪ አስፈላጊውን የደህንነት መሳሪያ በማሟላት የሰራተኞቹን ህይወት ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት መዘንጋት የለበትም፡፡    

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም