የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳል

61

አዲስ አበባ  ጥር 13/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጨዋታ ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳል።

ነገ በክልል ስታዲየም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ስሁል ሽረ ከድሬዳዋ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና ከመከላከያ እና መቐለ ሰብአ እንደርታ ከኢትዮጵያ ቡና  ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽ ያወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል።

እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከፋሲል ከተማ፣ አዳማ ከተማ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና ሀዋሳ ከተማ ከደቡብ ፖሊስ ረቡዕ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት ይጫወታሉ።

ፕሪሚየር ሊጉ ሐሙስ ቀጥሎ ሲውል ሁለት ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋር ከወላይታ ድቻ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በጅማ ስታዲየም ይገናኛሉ። በአዲስ አበባ ስታዲየም ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ግርጌ ላይ የሚገኘውን ደደቢትን ይገጥማል።

ፕሪሚየር ሊጉን ኢትዮጵያ ቡና በ22 ነጥብ አንደኛ ሆኖ ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስና ፋሲል ከተማ በእኩል 18 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው 2ኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ሀዋሳ ከተማና ሲዳማ ቡና በእኩል 17 ነጥብ አራተኛና አምስተኛ ደረጃን ሲይዙ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ16 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ስሁል ሽረ፣ ጅማ አባ ጅፋር፣ ደቡብ ፖሊስና ደደቢት ደግሞ ከ13ኛ እስከ 16ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተቀምጠዋል።

የኮከብ ጎል አግቢነቱን የአዳማ ከተማ ዳዋ ሁቴሳና የሲዳማ ቡና አዲስ ግደይ በሰባት ግቦች ሲመሩ፣ የመከላከያ ምንይሉ ወንድሙ በ6 ጎል፣ የሀዋሳ ከተማ ታፈሰ ሰለሞንና እስራኤል እሸቱ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡና አቡበከር ነስሩ በተመሳሳይ 5 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም