በአማራ ክልል የጥምቀት በዓል ያለ ምንም የጸጥታ ችግር መከበሩን ፖሊስ ገለጸ

49

ባህር ዳር ጥር 11/2011 በአማራ ክልል በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የጥምቀት በዓል በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ የኮሙኒኬሽን ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ሰኢድ አህመድ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓሉ በክልሉ ሁሉም ዞኖችና ከተሞች ያለ ምንም የጸጥታ ችግር ተከብሯል።

ኮሚሽኑ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ በየደረጃው ያሉ የጸጥታ አካላት ከወጣቱ ጋር ተቀናጅተው መንቀሳቀሳቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው አስረድተዋል።

የፀጥታ መዋቅሩ ከወጣቱ ጋር በመተባበርም ትናንት ታቦታትን በሰላም አጅቦ ወደ ባህረ ጥምቀት ከማድረስ ጀምሮ ዛሬ ተመልሰው ወደ ዐብያተ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።

''ኅብረተሰቡ በዓሉ በሰላም አንዲጠናቀቅ ክፍተኛ ፍላጎትና ትብብር አሳይቷል'' ብለዋል።

በዓሉ  ወደ ፊት ለሚከበሩ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በተደራጀ አግባብ ለማክበር ትምህርት እንደተገኘበት አስረድተዋል።

ወጣቶች ላበረከቱት አስተዋጽኦም ረዳት ኮሚሽነሩ ምሰጋና አቅርበዋል።

በክልሉ በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው የክልሉ ከተሞች መካከል ጎንደር ፣ ባህርዳርና ላሊበላ ይገኙበታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም