የጥምቀት በዓል ለሰላምና ለአንድነት

1462

(ደሳለው ጥላሁን-ኢዜአ)

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ወቅትን ጠብቀው ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው የጥምቀት በዓል፡፡ እንደ እምነቱ ሊቃውትን ትርጉሜ ጥምቀት ማለት መነከር ፣መታጠብ ፣ መረጨት ማለት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት መካከል አንዱ የሆኑት መጋቢ ሀዲስ መኮንን ወልደ ትንሳኤ የጥምቀት በዓል የአከባበር ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ እንደሚሉት ቤተ ክርስቲያኗ የጥምቀት በዓልን የምታከብረው ከሌሎች በዓላት በተለየ ሥነ ሥርዓት ነው፡፡ በዓሉን የተለየ የሚያደርገው በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ታቦታት ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ወንዝ ወርደው ለማረፊያ በተዘጋጀላቸው ቦታ ያድራሉ፡፡

ህዝበ ክርስቲያኑ በነቂስ ወጥቶ ታቦታቱን በማጀብ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በመሄድ ያከብራሉ፡፡ ካህናት ሌሊቱን በማህሌት ስብሐተ እግዚአብሄር ሲያደርሱ ቆይተው የቅዳሴው ስነ ሥርዓት በመንፈቀ ሌሊት ተጀምሮ ከሌሊቱ 9፡00 ሰዓት ይፈጸማል፡፡

ጥር 11 ቀን ጠዋት በባሕረ ጥመቀቱ ላይ ጸሎት ይደረግና ውኃው ይባረካል፡፡ ህዝቡም በተባረከው ውሃ ይረጫል፡፡ ከዚህ የሚቀጥለው ታቦታቱን የተሸከሙ ካህናት ከድንኳኑ ወጥተው ለዛማሬ ማህሌት በተዘጋጀው አውደ ምህረት ላይ ይቆማሉ፡፡

መዘምራኑ በዓሉን በተመለከተ ቃለ ማሕሌት በመቃኘት ያሸበሽባሉ፡፡ ከዚያ በወጣት መዘምራን ዝማሬ ጉዞ ወደ ቤተክርስቲያን ይሆናል፡፡ በዋዜማው እንደተደረገው ሕዝቡ ሁሉ በቋንቋው፣ በባህሉ መሰረት እያሸበሸበ በዕልልታና በሆታ በማጀብ ይጓዛል፡፡

በሀገራችን ታቦት ተሸክሞ ፣ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ታሪክ በመከተል አፄ ነዖድም(1486 – 1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነ ሁሉ ታቦተ ህጉን ወደ ጥምቀተ– ባህሩ በሚወርድበት ጊዜ እና ከጥምቀተ – ባህሩ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ መውረድ እና መመለስ እንዳለበት አዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ በአዋጁ መሰረትም ህዝቡ በየአመቱ ታቦተ ህጉን በማጀብ ወንዶች በጭፈራ እና በሆታ፣ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ሲያከብሩ ኖረዋል፡፡

ይህ የአከባበር ስነ ሥርዓት እንግዲህ በየጊዜው ወቅቱን ጠብቆ ዛሬም እንደ አምና እና ታች አምና እየተከበረ ነው፡፡

የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግ እና ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ህብረ– ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡ ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍር እና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበት እና በጋራ የሚጫወትበት ዕለት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ህዝበ ክርስቲያኑ ይህንን በዓል ዘር እና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ህዝብን ያቀራርባል፤ የመረዳዳት ባህልንም ያሳድጋል፡፡

ወጣቱ ትውልድ፥ በሥልጣኔ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በጠንካራ ክርክርና ምክንያታዊ በሆነ አስተሳሰብ የሚመራ፣ በዘመነ ሉላዊነት በዚህም በዚያም ጎታችና ጎትጓች በበዛበት ሁኔታ ውስጥ ኑሮውን የሚመራ ቢሆንም፤ባህሉን፣ ሃይማኖቱን፣ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ጠብቆ ቀደምት አባቶቹ ሲያከብሩ የኖሩትን የጥምቀት በዓል ከመቼውም ጊዜ በተሻለና ባማረ መልኩ እንዲከበር የሚያሳየው ትጋትና ጥረት የሚያስመሰግነው መሆኑን በዙኃኑ የሚስማሙበት ነው፡፡

“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንደተባለው ሁሉም የእምነቱ ተከታይም ሆነ በበዓሉ ላይ የሚታደም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኝ በተለያዩ ቀለማት ባሸበረቁ የባህል ልብሶች አምሮና ደምቆ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ ያከብራል፡፡

ለሰላም፣ለመቻቻልና ለአንድነት ተምሳሌት ለሆነችው ኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አንዱና ዋነኛው ነው ቢባል ያንስበታል እንጅ አይበዛበትም፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ ሁከትና ብጥብጦች የአገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና ተቻችሎ የመኖር የቆየ ባህል ቢሸረሽርም ጥምቀትን የመሰሉ ሃይማታዊ በዓላትን ለተመለከተ የኢትዮጵያውያን አንድነት ላይፈታ የተገመደ፣ላይቆረጥ የታሰረ መሆኑ እሙን ነው፡፡

የዘንድሮው የጥምቀት በዓልም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተከበረው በዓለ ጥምቀት አዲስ አበባን ጨምሮ በጎንደር አፄ ፋሲል መዋኛ ፣ በላልይበላ ፣ በመቀሌ ፣ በአክሱም ፣በማይጨው፣ በጋምቤላ፣ ፣ በባህርዳር፣ በሀዋሳና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ተከብሯል፡፡

የቤተክርስቲያን አባቶች፣ ምዕመናን፣የተለያዩ ሀገራት ቱሪስቶች ፣ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮች እና ባለስልጣናት በተለያዩ ቦታዎች በተከበረው የጥምቀት በዓል በመገኘት በጋራ አክብረዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የጥምቀት በዓልን አስመልክቶ ለክርስትና እምነት ተከታዮች ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ጥምቀት ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ከሚያሳዩት በዓሎች አንዱ መሆኑን መጥቀሳቸው የጥምቀት በዓል ለኢትዮጵያውያን አንድነት፣ሰላምና መቻቻል ያለውን ፋይዳ የሚያሳይ ነው፡፡

“ቀደምት አባቶቻችን እና እናቶቻችን ይህንን በዓል እንድናከብር ሥርዓት ሲሰሩ በአንድ በኩል በትህትና ስለ ዝቅ ማለት እና ስለ መለወጥ፣ በሌላም በኩል ደግሞ ስለ መደመር ሊያስተምሩን የፈለጉ ይመስለኛል”  ሲሉ መግለጻቸው በእርግጥም ለዘመናት ዛይበረዝ የቀጠለው ሃይማኖታዊ በዓል የሰላም፣ የአንድነት፣የትህትና ምንጭ መሆኑ እውን ነው፡፡፡

የጥምቀት በዓል  የመለወጥ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለወጡት ውስጥም አንዱ ውኃ እንደሆነና የሰው ልጅ ከውሃው መለወጥ በፊት በነበረው ታሪኩ ውኃን የሚያስታውሰው በቁጣ መሣሪያነቱ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

“የሰው ልጅ በውኃ ጠፍቷል፤ ክርስቶስ የመዓቱን ውሃ የምህረት አደረገው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውን በክፉ ሚያስታውሷቸው  ሞያዎችና ተቋማት በመኖራቸው እነዚህን የክፋት መታወሻዎች እንደ ውኃው ሁሉ ወደ በረከትነት በመቀየር ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ እንዲሰሩ በማድረግ መለወጥ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

“ለጥምቀት ያልሆነ—” ነውና ቅሉ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ መሰናክሎች ውስጥ ቢያልፉም በተለይ የእምነቱ ተከታዮች ዛሬም ድረስ  የጥምቀት በዓልን በታላቅ ድምቀት እያከበሩ ነው፡፡

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለክርስትና እምነት ተከታዮች በሳተላለፉት መልዕክት “በጊዜያዊ እና አልፎ ሂያጅ ነገሮች ላይ ማተኮር ውጤታችንንም ታሪካችንንም ጊዜያዊ አድርጎት ስለሚቀር በልፋታችን፣ በትግላችን እና በብርታታችን የምንቋደሰው ድል የሁላችንም የመሆኑን ያህል ተግዳሮት እና ፈተናውም የሁሉም ኢትዮጵያ ልጆች እንቅፋት መሆኑን በመረዳት እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር እና በመደመር ልንሻገረው ይገባል”ያሉት፡፡

የታሪክ ድርሳናት እንደሚያትቱት ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው፣ በአንድነታቸውና በሰላማቸው መቼም ቢሆን አይደራደሩም ጊዜያዊ ችግሮች ቢከሰቱም እነዚህን ችግሮች በራሳቸው የሚፈቱባቸው አኩሪ ባህሎች አሏቸው፡፡ ይሄም ትናንት ነበር፣ ዛሬም አለ፣ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡

እንደ ጥምቀት ሁሉ ለአንድነት፣ለሰላምና  ለመቻቻል አስተዋጽኦ ያላቸው ሃይማኖታዊ በዓላትን ለማክበር ሰላም ከማነኛውም ነገር በላይ ወሳኝ ነው፡፡

ለዚህም ነው ዛሬ  በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ “ኢትዮጵያዊያን ከመለያየት ይልቅ የፈጣሪ ክቡር ሥራ ለሆነው የሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት ትኩረት አንዲሰጡ”  አባታዊ መልዕክት ያስተላለፉት፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በዘርና ቋንቋ በመከፋፈል የሚስተዋለውን ግጭት እርሱንም ተከትሎ መግደልንና ማፈናቀልን ጨምሮ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ያፈነገጠ፣ ኢትዮጵያዊ ገፅታ የሌለው ጎጂ ተግባር መሆኑ ያስረዱት ፓትሪያርኩ የኢትዮጵያዊያን የማንነት መገለጫ ዘርና ቋንቋ ወይም ክልል ሳይሆን የእግዚያብሔር ታላቅ ሥራ የሆነው የሰው ፍጡር መሆኑን ሊገነዘቡ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

“በቀል ሰላምን አይወልድም፤ ይቅርታ ግን ምድርን ሁሉ በፍቅር ያጥለቀልቃል” ያሉት አቡነ ማቲያስ  በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አንገብጋቢው ጉዳይ አንድነት፣ ሰላምና የሰብአዊ መብት መከበር በመሆኑ በተለይ ወጣቱ በማስተዋል መንገድ ሊጓዝ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

በዓሉ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በኦሮሚያ ክልል አዳማ መስቀል አደባባይ ባህረ ጥምቀት ሲከበር በበዓሉ ላይ የተገኙት የምስራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  አቡነ ጎርጎርዮስ ስለ ሰላምና አንድነት አስፈላጊነት ለበዓሉ ታዳሚዎች አባታዊ ምክር ሰጥተዋል፡፡

ሊቀ ጳጳሱ በዓሉ የአንድነት፣ የአብሮነትና የደህንነት ተምሳሌት መሆኑን በመግለጽ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዓሉን ሲያከብር ለአገር ሰላም፣ አንድነትና ልማት በጋራ መስራትን እንደሚገባው  አሳስበዋል።

በተመሳሳይ መልኩ በትግራይ ክልል ማይጨው በተከበረበት ወቅት በበዓሉ የታደሙት የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ዴዮስቆሮስ ስለ ሰላም፣ስለ አንድነትና መቻቻል አጽኖት ሰጥተው ለበዓሉ ተሳታፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

“ሰላም ከሌለ የጥምቀት በዓልን እንዲህ ተሰባስበን ማክብር አንችልም” ያሉት አቡነ ዴስቆርዮስ፣ የእምነቱ ተከታዮች ለሰላም ዘብ መቆም እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

ግጭት ልማትን ሳይሆን፤ ጥፋትን እድገትን ሳይሆን ውድመትን እንደሚፈጥር የተናገሩት አቡነ ዴስቆርዮስ፣ የሕዝቡ ፍላጎት ሰላም በመሆኑ የፖለቲካ መሪዎች ልዩነታቸውን በማጥበብ ለሰላምና እድገት መነሳት እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ-ስርአቶች በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል በድምቀት የተከበረ ሲሆን በበዓሉ ላይ የተገኙት ቤተ ሊቀ-ጳጳስ ዘካቶሊካዊያን እንደራሴ አባ ተስፋዬ ወልደማርያምም  የእምነቱ ተከታዮች ለሰላም፣ ለአንድነት፣ እርስ በእርስ ለመከባበር ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል፡፡

በዚያም ተባለ በዚህ ሰላም ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን አስፈላጊ ነው፡፡ ጥምቀትንም ሆነ መሰል ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል ለማክበር ሰላም ግድ ይላል፡፡ የምቀት በዓል ለኢትዮጵያውያን አንድነትና ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌት ሆኖ እንዲቀጥል ሰላም ያስፈልጋል፡፡

ከሁሉም በላይ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የኢትዮጵያ ወጣት ዘብ ሊቆም ይገባል፡፡ የከተራና ጥምቀት በዓል በየአመቱ ሲመጣ ታቦታት ወደ ማረፊያቸው የሚሄዱበትንና የሚያርፉበትን ቦታ ዘር፣ ኃይማኖት፣ ዕድሜ ሳይለይ  በትብብር የሚያጸዳና የሚያስውበው ወጣት ለሰላም ለአንድነትና ለመቻቻል ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰራ ይገባል፡፡ ሰላም፡፡