'አፍረን ቀሎ' የሙዚቃ ባንድ አባላት ከረጅም ጊዜ የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ወደ አገር ቤት ተመለሱ

164

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 በአፋን ኦሮሞ የመጀመሪያ እንደሆነ የሚነገርለትና " አፍረን ቀሎ" በሚል ስያሜ የሚታወቀው የሙዚቃ ባንድ ከረጅም ዓመታት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ዛሬ አዲስ አበባ ገባ።

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1962 በድሬዳዋ ከተማ የተመሰረተው አፍረን ቀሎ አንጋፋውን የክብር ዶክተር አሊ ቢራን፣ አሊ ሸቦንና  አህመድ አሩንን ጨምሮ በርካታ ስመ ጥር የአፋን ኦሮሞ ከያኒያንን ያፈራ አንጋፋ የሙዚቃ ቡድን ነው። 

የሙዚቃ ባንዱ አባላት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ሲደርሱ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ እና ሌሎች የፓርቲውና የመንግስት ባለስልጣናት እንደዚሁም አርቲስቶች፣ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂዎቻቸው ተቀብለዋቸዋል።

ከቡድኑ ጋር የመጣው ጋዜጠኛ እና አርቲስት ጃፋር አሊ በዚሁ ወቅት "በብዙ ዜጎች መስዋእትነት የተገኘውን ለውጥ ለመገደፍ እና ለማጠናከር ነው ወደ አገራችን የተመለስነው" ብሏል።

"ከአገር ቤት የወጣነው አገራችንን ጠልተን ሳይሆን ጭቆና በዝቶብን ነው፤ ነገር ግን በአገር ውስጥ ያሉ ህዝቦች በጀግንነት በመታገል ከቤተሰቦቻችን ጋር ስላቀላቀሉን ምስጋና ይገባቸዋል፤"  ሲልም ተናግሯል።

አክሎም "ከዚህ በፊት የነበረውን ጭቆና ስቃወም የተጠቀምኩበትን ሙያዊ አቅም አሁን ደግሞ ድህነትን ለመዋጋትና ለውጡን ለማስቀጠል ዓላማ አውለዋለው" ሲልም አርቲስት ጃፋር ቃል ገብቷል። 

የኦሮሞ ህዝብ አሁን ያለውን ለውጥ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹ ጋር በመሆን ጠብቆ ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ እንዳለበትም አሳስቧል። 

'ዱምቡሼ ገላ' በሚለው ሙዚቃው የሚታወቀውና  ከ30 ዓመት የውጭ አገር ኑሮ በኋላ ወደ አገር ቤት የተመለሰው አርቲስት አሊ ሸቦ  "ከአገራችን የወጣነው በደረሰብን በደል ነው፤ አሁን ደግሞ በዜጎች ትግል ወደ አገራችን ገብተናል" ብሏል።

አርቲስት አሊ ሸቦ የተለያዩ የዘር ጭቆና ዘፈኖችን በማቀንቀን፤ በኢትዮጵያ የነበረውን የፖለቲካ ስርዓት በመቃወምና የህዝብ ትግልን በማነቃቃት ተግባሩ ይታወቃል።

በአቀባበሉ ላይ የተገኙት አባ ገዳ ጎባና ኦላ በበኩላቸው ረጅም ዓመታት ከአገራቸው ርቀው የነበሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ወደ እናት አገራቸው መመለሳቸው የሚያስደስት ነገር መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም አርቲስቶቹ ለረጅም ዓመታት የኦሮሞን ኪነ ጥበብ ከማሳደግ በተጨማሪ ህዝቡን ለእኩልነት እንዲታገል በማነሳሳት ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል።

አሁን የተገኘውን ለውጥ ለማስቀጠል እና ሁሉም ዜጋ በእኩልነት እንዲኖር ያሁኑ ትውልድ ከቡድኑ አባላት ፅናት ብዙ ነገር መማር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የኦዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ አርቲስቶቹ የኦሮሞ ሙዚቃን ጨምሮ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ በመሆኑ ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

በብዙዎች መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ ዜጎች የፈለጉትን አስተሳሰብ በነጻነት ማራመድና መግለፅ የሚችሉበትን ስርዓት እየፈጠረ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ዓለሙ "አገራዊ ለውጡን ለመቀልበስ የሚሰሩ ተቋማትንና ግልሰቦችን ህዝቡ ሊታገላቸው ይገባል" ብለዋል።

ዛሬ ወደ አገራቸው የገቡትን ጨምሮ አዳዲስና ነባር የኦሮሞ አርቲስቶችን የሚያሳትፍ የሙዚቃና የጥበብ ኮንሰርት ጥር 18 ቀን 2011ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም