በበዓላት ወቅት በወጣቱ ዘንድ የሚታየው ትጋት በአገራዊ ጉዳዮች ላይም ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል አቅም እንዳለው ያሳያል ተባለ

95

አዲስ አበባ ጥር 11/2011በኢትዮጵያ በየአመቱ የከተራና ጥምቀት በዓል  ሲከበር በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ልዩ ገጽታዎችን ማስተዋል እየተለመደ መጥቷል።

ከእነዚህ ልዩ ገፅታዎች መካከል ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ልዩነት ታቦታት የሚያልፉባቸውን መንገዶች እና የሚያርፉባቸውን ቦታዎች  በተለያዩ አካባቢዎች በጋራ ማጽዳት እና ለምእመናኑ የሚያደርጉት መስተንግዶ ይጠቀሳል።

በዚህ ወቅት በተለይ ወጣቶች ማህበረሰቡን ለማገልገል፣ በዓሉ ሰላማዊና የደመቀ እንዲሆን የሚያሳዩት ተነሳሽነት፣ የባለቤትነት መንፈስና ትጋት የሚያስደንቅ እንደሆነ ነው ምእመናንም ሆኑ ሌሎች ታዛቢዎች የሚገልፁት። 

በዘንድሮው የከተራና የጥምቀት በዓልም ከዋዜማው ጀምሮ የእምነቱ ተከታይ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ታቦታት የሚያርፉበትን ቦታ ሲያጸዱ ተስተውሏል።

እናም ይህ ከፍተኛ የሆነ ማህበረሰባዊ ኃብት በተለይ ወጣቱ ለውጥን ለማምጣት ልዩ አቅም ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ በመሆኑ፤ ይህ አቅም በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይም እንዲንፀባረቅ የሚሹት በርካቶች ናቸው።

ዛሬ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የኢዜአ ሪፖርተር በአዲስ አበባ በጃንሜዳ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የእምነቱ ተከታዮች የሚሉትም ይህንኑ ነው።

በጥምቀትና ከተራን በአል በጸጥታ፣ በጽዳት፣ አቅመደካሞችን በመርዳት በህብረት የሚሰሩ ተግባራት ወጣቱ በሌሎች የእለት ተእለት ህይወቱ ውስጥም ሊተገብራቸው እንደሚገባ  አስተያየት ሰጪዎቹ መክረዋል። 

እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በጥምቀት በዓል የሚያሳየውን ትብብርና አንድነት በተሰማራበት የስራ መስክም መተግበር ይገባዋል የሚል ሀሳብ አንስተዋል።   

ከነዋሪዎቹ መካከል ወጣት ሰማኽኝ ተስፋው  ታቦት ሲወጣ የማይተዋወቀው የተለያየ ሰፈር ልጆች ለአንድ አላማ ሁሉም ሲሰሩ ይታያል ፤ ታቦት የሚሄድበትን መንገድ በማጽዳት ምንጣፎችን ተራ በተራ በመሸከም ይሰራል፤ ይህን የተቸገረን ሰው በመርዳት፣ በሰፈራችን በመተጋገዝ ሁላችንም አንድ ስለሆንን ባለመከፋፈል ለአንድ አላማ ሁላችንም በፍቅር መስራት አለብን ብላል፡፡

አቶ ባዛዝን ተረፈ በበኩላቸው ከጎናችን ያለው ሌላ ኢትዮጵያዊ ፣ የተለየ እምነት የተለየ ቀለም፣ የተለየ ብሔር ያለው ነው ግን አንድ ሰዎች የሆንን መሆናችንን በእየለቱ ለእራሳችን ማሳወቅ ከዛ በተጨማሪ ደግሞ ለአገራችን በምንችለው መንገድ ባህላችንን የሚያሳዩ ነገሮችን አመት ብቻ እየጠበቅን ብቻ ሳይሆን በአሰራሮቻችንም በተግባራችን አገራችንንን እያሰብን ኢትዮጵያዊነትን አንድነትን ጎልቶ መታየት ነው ያለበትሲሉ አስተያየታቸውን ሰትተዋል፡፡

ከዋዜማው ጀምሮ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብ የሚሰሩ ተግባራትን ቀስ በቀስ የኑሯችን አካል በማድረግ አገራችንን መለወጥ እንችላለን የሚል ሀሳብም አንስተዋል።  

አስተያየት ሰጪዎቹ በጥምቀት በአል ጥቁር፣ ነጭ፣ ኃይማኖት ሳይል በፍቅር በአንድ ቦታ የመሰብሰቢያ ቀን በመሆኑ ይህንን ፍቅር ወደ መደበኛ እንቅስቃሴያችን እንቀይር ብለዋል። 

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩትና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ከሚያሳዩት በዓሎች አንዱ ነው። 

ዛሬ በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተከበረው የጥምቀት በአል ኃይማኖታዊ ስርዓትና የተለያዩ ባህላዊ ትዕይንቶች ተከናውነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም