ጥምቀትን በትዝታ

1422

አስማረች አያሌው /ኢዜአ/

አቶ ጨፍሮ ጃርሶ ከ1960 ጀምሮ ከተለያዩ ነጋዴዎች ጋር በመመላለስ አዲስ አበባን እንዳወቋት ይናገራሉ። ከ1970 ጀምሮ ደግሞ የመንግስት ሰራተኛ ሆነው አዲስአበባ መኖር መጀመራቸውን ያወሳሉ፡፡

ጥምቀትን በአዲስ አበባ እንዴት ያሳልፉ እንደነበር አጫውተውናል፤ “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” እንደሚባለው ለጥምቀት አልባሳት ተዘጋጅቶ የሚቀመጥበት ሁኔታ መኖሩን ይገልፃሉ፡፡

“አባቶቻችን ለጥምቀት ልብስ ያዘጋጃሉ፣ ልብስ ይከተታል ፣አየር ባየር አይደለም የሚለበሰው  የክት ሊኖር ይገባል፣ የክት ልብስ የሚባለውም ለዛ ነው፡፡”ይላሉ።

በአዲስ አበባ ያሉ ብሄር ብሄረሰቦች የጥምቀት በአልን አስታከው ባህላቸውን  የሚያንፀባረቁበት  ሁኔታ እንደነበርም በትዝታ ወደ ኋላ በመመለስ  ይገልጻሉ።  

ጥምቀትና መተጫጨት   

የጥምቀት በአል ወጣቶች የሚፈላለጉበት መሆኑን የሚገልፁት አቶ ጨፍሮ “በኛ ጊዜ ሆነ ተብሎ  ጓደኛና ትዳር መፈለጊያ ነው፣ ክብ ሰርተው ሴቶች ለብቻ ወንዱም ለብቻ ሆነው ይጨፍራሉ፤ ወንዶቹ ሴቶቹን ቀለበት ውስጥ ያስገባሉ፣ወንዱ የፈቀዳት ላይ ሎሚ ይወረውራል፡፡ ወንዶች መጀመሪያ ከኋላ ነው የሚቆሙት፣ የተፈቀደለት መሃል ይገባል አብሮ ይጨፍራል፣መበጥበጥ መረበሽ የለም፡፡”

ጥምቀት ላይ የተገናኙ ወዳጆች ግንኙነታቸው ዘላቂ ነው የሚሉት አቶ ጨፍሮ መሰረታዊ ባህላዊ አካሄድ አላቸው፣ ግንኙነታቸውን ያሳውቃሉ፤ ወደ ቤተሰብም ሽማግሌ  ይላካል፡፡

ልጅቱ በአይን ስለተመረጠች ቤተሰብም የሁለቱን ጓደኞች ጀርባ ያጠናል፣ ዝምድናቸው ከሰባት ቤት ዝቅ ያለ እንዳይሆን ፣ ከሰባት ቤት ዝቅ ያለ ዝምድና ካለ ይቀራል፡፡ ሴቷ ካልሆነ ሰው እንዳትወድቅም ቤተሰብ የራሱን ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ በዚያን ዘመን ሌላው  የመተጫጫ ቦታ ገበያ መሆኑንም አጫውተውናል፡፡

ጃንሜዳና ጥምቀት

ጃን ሜዳ በአለም ታሪክ የሰሩ ሰዎችን ያፈራ ቦታ ነው፣ አዋጅ የሚነገርበትና ህዝብ የሚሰበሰብበት ስፖርትም የሚዘወተርበት ሃገራዊ ውክልና ያለው ቦታ እንደሆነም  አቶ ጨፍሮ ነግረውናል።  

ጃን ሜዳ በተለያየ ጊዜ ለልማት እየዋለ፤  እየጠበበ መምጣቱ ያሳስባቸዋል፡፡ እንደ ጥንቱ ቢመለስም ምኞታቸው ነው፤ አበበ ቢቂላ እና ሌሎች ነባር ስፖርተኞች ከጃንሜዳ ነው የወጡት ይላሉ፡፡

“ጃን ሜዳ ሳይሆን “ጃድ ሜዳ” ነው የሚባለው ይህም መፎከሪያ፣መፈንጫ፤ መደሰቻ ነው። ድል ከሆነ የብስራት መነገሪያ ህዝባዊ ሜዳ ማለት ነው” እናም ድሮ ሁሉም በር ክፍት ሆኖ ያለመገፋፋት ጥምቀትን እናከብራለን ብለዋል፡፡

ጥምቀትና የድሮ ወጣት

አቶ ጨፍሮ እንዳሉት በድሮው ግዜ በአሉ ሲከበር የእለት ግጭት እንኳን ቢኖር ፀቡ አይከርም፤ ጠላትነትና ፍርድ ቤት አይቋቋምም፤ በነጋታው አብረው መጫወት ይጀምራሉ፡፡

“በገና  ጨዋታም እንደዚሁ ነው ፣ሰዎች ቢጋጩ እንኳን መልሰው ጠላ ቤት ይገናኛሉ፤ ወዲያው እርቅ ይሆናል፣ሳር ቅጠሉ ፍቅር ነው፡፡ የዛን ቀን ነው እንጂ በነጋታው ለጥምቀት እንዲህ አድርገኸኝ ነበር አይልም፤ በዚህ እኔም አልፌበታለሁ ደርሼበታለሁ’’ ነው ያሉት።

የአሁን ወጣት ባህሉን ላለመተው የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ቢሆንም ጉራማይሌነት ይስተዋልበታል ያሉት አቶ ጨፍሮ ለማገልገል ያለው ፍላጎት ጥሩ ቢሆንም ውስጣዊ መሆን እንደሚገባው ግን ሳይጠቅሱ አላለፉም። 

“ወጣቱ በራሱ ተነሳሽነት እንጂ “ወደ እኔ ኑ” የሚለው አካል አላገኘም፣ ወጣቱ ጥሩ እየሰራ ነው ግን ማምሻውንም ሊያሳምር ይገባል፤ የሃይማኖት አባቶች ጣልቃ ገብተው ያልተፈለጉ ባህሪያትን ማረቅ ይገባቸዋል” በማለትም ይመክራሉ።

ጥሩ ነገር በመስራትና በማሳየት ወጣቶችን ማስተካከል ይቻላል የሚሉት አቶ ጨፍሮ  በፍቅር ማመን አለብን ይላሉ፡፡

የጥምቀት ገጠመኝ

አቶ ሰለሞን ግርማ የጥምቀት በአልን ለማክበር በወጡበት አጋጣሚ በ1988 ዓ.ም የትዳር አጋራቸውን መተዋወቃቸውን ያወሳሉ፡፡

“አስቤው ባልወጣም በጥምቀት ቀን ከልጄ እናት ተዋውቄያለሁ” ይሄ የማልረሳው የህይወቴ ገጠመኝ ነው ይላሉ፡፡

በልጅነት እድሜያቸው ጥምቀትን ጃንሜዳ ሲያከብሩ የሃርሞኒካና የተለያየ ባህላዊ  ጭፈራዎች የበአሉ ድምቀት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሰለሞን  አሁን ላይ እንዲህ አይነቱ ጭፈራ እየቀረ መምጣቱን ይገልጻሉ።  

ለአሁን ወጣቶች  የቀደሙት አባቶችና እናቶች ግንዛቤ ያለመስጠት ክፍተት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸው ነባር ባህሉን ለመመለስ ሚዲያ በስፋት መስራት ይጠበቅበታል ይላሉ። 

ያኔ “የተሸለመው ረዣዥም እንጨት ሁሉ ይታወሰኛል፣ያ ምናልባት ከጸጥታው በተያያዘ ቀርቶ ይሆናል” ብለዋል፡፡

ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ…

ወይዘሮ ወይንሸት ሙሉነህ ጥምቀትን ባለፉት 37 አመታት በጃንሜዳ ማክበራቸውን ያስታውሳሉ፡፡

በጥምቀት ለሃበሻ ልብስና ለፀጉር ስሬት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጡ የተናገሩት ወይዘሮ ወይንሸት  “ሰው ባለው ይኮራል እንደሚባለው እኔም ለጥምቀት እጥብ እጥን አድርጌ የማዘጋጀው የክት ልብስ አለኝ” ይላሉ፡፡

ወጣቱ ወደ ሃገር ልብስ ፊቱን እየመለሰ መሆኑን የሚናገሩት ወይዘሮ ወይንሸት ሴቶቹም በሃገር ልብስ ወንዶቹም  የተለያዩ ቲ-ሸርቶች በጥበብ በማሰራት ባህሉን የሚያወሳ ነገር ያደርጋሉ፤ “የአባትና እናቶቻችንን ባህል ይዘን ቆይተናል ባህሉ አልጠፋም”በማለት ነው የሚገልጹት።

የጃንሜዳ ጨዋታዎች

ወጣት ተዋህዶ ከበረ ጃንሜዳ የኳስ፣ የበአል ጨዋታዎች፣ የሞተርና የፈረስ ዝላይ ጨዋታዎች እንደነበሩ ያስታውሳል፤ አሁን አሁን ባህላዊ ይዘቱን ወደ ጎን በመተው ይበልጡን ሃይማኖት ተኮር እየሆነ መጥቷልም ይላል።  

ድሮ የቡድንና ባህላዊ ጭፈራዎች ነበሩ፤ አሁን ላይ እየቀሩ ነው ያለው ተዋህዶ የራያ ጭፈራዎች ከቀጨኔ አካባቢ በሚመጡ ሰዎች የሚያሳዩ አሉ እነሱን አስታውሳለሁ ብሏል ፡፡

በጥቅሉ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ ባሻገር ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሴቱ በርካታ በመሆኑ በተለይ በሀገራችን ላሉ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ ትስስር ወሳኝ ነውና ባህልና ቱሪዝም በባለቤትነት ወስዶ ከምሁራን፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ መስራት ይገባል መልዕክታችን ነው።