የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ-ስርአቶች ተከበረ

100

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በተለያዩ መንፈሳዊ ስነ-ስርአቶች በልደታ ካቶሊክ ካቴድራል በድምቀት ተከበረ።

በክብረ በዓሉ የእምነቱ ተከታዮች በጠዋት በመሰባሰብ በማህሌት፣ቅዳሴ፣በመንፈሳዊ መዝሙሮች፣በወጣቶችና ህፃናት መርሃ ግብር ተከውኖ ነው የተከበረው።

የቤተክርስቲያኗ ሊቀ-ጳጳስ ዘካቶሊካዊያን እንደራሴ አባ ተስፋዬ ወልደማርያም እንደገለጹት ምእመኑ በዓሉን ሲያከበር የትህትና መምህር የሆነውን የክርስቶስ ፈለግ በመከተል መሆን ይኖርበታል።

ይህም ለሰላም፣ለአንድነት፣እርስ በአርስ ለመከባበርና ለመነጋገር እንዲሁም አንዱ ለሌላው በማሰብ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

የጥምቀት በአል መንፈሳዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊ ይዘት እንዳለውም የጠቀሱት አባ ተስፋዬ ህዝበ ምዕመኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቹ እንዲጎለብቱ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል።

ጥምቀት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ቢከበርም በኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ግን የተለየና ልዩ ድባብ ያለው ነው።

በመሆኑም በተባበሩት መንግስታት ድርጀት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ ለሚደረገው ጥረት ቤተክርስቲያኗ የበኩሏን ጥረት እያደረገች መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሉ በሚከበረብት ልደታ ካቶሊክ ካቴድራል ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናት፣ ምዕመናንና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም