ኢትዮጵያዊያን መለያየትን ከመስበክ ይልቅ ለአንድነትና ሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ አቡነ ማቲያስ አሳሰቡ

74

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 ኢትዮጵያዊያን ከመለያየት ይልቅ የፈጣሪ ክቡር ሥራ ለሆነው የሰው ልጅ ሰላምና ደህንነት ትኩረት አንዲሰጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያሪክ አቡነ ማቲያስ ጥሪ አቀረቡ።

ፓትሪያርኩ ይህንን ያሉት በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል ለታደሙ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት  ተከታዮች  ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በዘርና ቋንቋ በመከፋፈል የሚስተዋለውን ግጭት እርሱንም ተከትሎ መግደልንና ማፈናቀልን ጨምሮ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ከሃይማኖታዊ አስተሳሰብ ያፈነገጠ፣ ኢትዮጵያዊ ገፅታ የሌለው ጎጂ ተግባር መሆኑንም ገልፀዋል።

በዘርና በነገድ መመካት ከንቱ መሆኑ በመጥምቁ ዘመነ ዩሃንስ መረጋገጡን በቅዱስ መፅሃፉ ላይ መመልከቱን አውስተው "ከእኛ በላይ ዘር የለም፤ እኛ ከሁሉም የተለየን ነን  ይሉ የነበሩት አይሁዳዊያን በዚህ አስተሳሰባቸው ሲጎዱ እንጂ ያገኙት አንድም ጥቅም የለም ብለዋል።

"ኃያሉ አምላክ ቋንቋን የፈጠረው ለመግባቢያ፣ የክልል ወሰኖችን ደግሞ ለመተዳደሪያ እንጂ የሰው ልጅ እንዲለያይባቸው አይደለም" ያሉት ፓትሪያሪኩ ኢትዮጵያዊያንም የማንነት መገለጫ ዘርና ቋንቋ ወይም ክልል ሳይሆን የእግዚያብሔር ታላቅ ሥራ የሆነው የሰው ፍጡር መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል ብለዋል። 

መገዳደል፣ ዜጎችን ማፈናቀልንና መዝረፍን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋለው ግጭት መቆም አንዳለበትም አሳስበዋል።

በተለያየ ጎራ ያሉ ኃይሎች ከኃይል የቃላት ውርወራን ጨምሮ የተለያዩ አፍራሽ ተግባራት በመቆጠብ አሉ የሚሏቸውን ችግሮች በውይይትና በመነጋገር ለመፍታት ቅድሚያ እንዲሰጡም ጠይቀዋል። 

በተለይ ወጣቶች የሚፈጽሟቸውን ማናቸውንም ተግባራት በማስተዋልና በጥንቃቄ መመርመር እንዳለባቸው ጠቅሰው በአፍራሽ ተግባር ተጠምደው ለታሪካዊ ስህተት ላይ እንዳይወድቁ ም አስጠንቅቀዋል። 

ኢትዮጵያዊያን ከመለያየት ይልቅ ለአንድነት፣ ሰላምና ፍቅር ቅድሚያ እንዲሰጡም ብፁዕነታቸው ጥሪያቸውን አቅርበዋል።  

"በቀል ሰላምን አይወልድም፤ ይቅርታ ግን ምድርን ሁሉ በፍቅር ያጥለቀልቃል" በማለት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ አንገብጋቢው ጉዳይ አንድነት፣ ሰላምና የሰብአዊ መብት መከበር መሆኑን አንስተዋል።

ሌላው ሁሉ ከእነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች በኋላ ሊመጣ የሚችል በመሆኑ በትእግስት መጠበቅ ይገባልም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የጥምቀት በአል በሃይማኖታዊ ሰርዓትና ሌሎች ባህላዊ ትእይንቶችን በማሳየት በርካታ የእምነቱ ተከታዮችና የውጭ አገር ጎብኝዎች በተገኙበት ተከብሯል።

ከጃንሜዳ ባሻገር በዓሉ በአዲስ አበባ በሚገኙ 75 ያህል ቦታዎች በርካታ የአቅራቢያ ቤተክርስቲያናት ታቦታትን በማሰባሰብ በልዩ ድምቀት ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም