ወጣቱ ዕደ ጥበብን እንዲያውቅ ወላጆች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው-አስተያየት ሰጪዎች

152

አዲስ አበባ ጥር 11/2011 ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያን ባህላዊ የዕደ-ጥበብ አሰራር እንዲያውቅ ወላጆች ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተራ በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።

የከተራ በዓል በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በሃይማኖታዊና ባህላዊ ስነ-ስርዓቶች ተከብሯል።

የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች በዓሉን ለማክበር ከቀኑ ሰባት ሰዓት ጀምሮ ነበር በተለያዩ ባህላዊ አልባሳት ተውበው ወደ ጃንሜዳ መትመም የጀመሩት።

ከተለያዩ አብያተ-ክርስቲያናት ታቦታቱን አጅበው ወደ ስፍራው የመጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዝማሬዎች፣ ባህላዊ ጭፈራዎችና ጨዋታዎችም የከተራው ድመቀቶች ሆነዋል።

ጥምቀትና የአገር ባህል ልብስ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንደመሆናቸው በርካታ ታዳሚያን የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን ባህላዊ አልባሳት ለብሰው ነው ከተራን ያከበሩት።

ጥምቀት ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባሻገር የተለያዩ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸውን ለሌሎች የሚያስተዋውቁበት መሆም ሌላው ድምቀት ነው።

''ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ'' እንደሚባለው በየደረጃው ያለው የህብረተሰብ ክፍል የክት ልብስ ለብሶ አምሮና ደምቆ ከተራን ለማክበር በጃንሜዳ መታደሙም ለዚህ ነው።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የበዓሉ ታዳሚዎችም የኢትዮጵያ መለያ የሆነውን የባህል ልብስ አሰራር ለትውልድ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ብለዋል።

ከጥጥ አፈታተል ጀምሮ እስከ ሸማ ስራ ያለው ተግባር ወጣቱ ትውልድ ዘንድ መረሳቱንም ነው የገለጹት።

ይህ ደግሞ የወላጆች ቸልተኝነት መሆኑን ያነሳሉ።

ከቀጨኔ መድሃኔዓለም አካባቢ ከተራን ለማክበር የመጡት ወይዘሮ እታገኝ አንዳርጌና እየሩሳሌም ማርቆስ በሚኖሩበት አካባቢ የሸማ ስራ የሚሰራ ቢሆንም ለስራው ትኩረት እንደማይሰጡት ነው የገለጹት።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያት ወላጆቻቸውም ሆነ የተማሩበት ትምህርት ቤት የእደ-ጥበብ ሙያ እንዲያውቁ እገዛ አለማድረጉን አንስተዋል።

ከስድስት ኪሎ ከተራን ለማክበር ጃንሜዳ የተገኙት ወይዘሮ የሺወርቅ ጌታሁን ''ጥጥ እንዴት እንደሚፈተል አይደለም ልጆቼ እኔም አላውቅም'' ይላሉ።

''አያት ቅድመ አያቶቻችን በእጃቸው ፈትለው ለቤተሰቡ የሚሆን ልብስ ያሰሩ ነበር የሚል ታሪክ ከመስማት ባለፈ የኔ ወላጆች ይህን አላስተማሩኝም'' የሚሉት ወይዘሮዋ የገበያ በመግዛት የባህል አልባሳትን እንደሚለብሱም ነው የተናገሩት።

ይሁንና ሸማ ስራ የኢትዮጵያ የባህል መገለጫ እንደመሆኑ ስለ አሰራሩ በቂ እውቀት ሊኖራቸው ይገባ እንደነበር ነው በቁጭት ያነሱት።

ወይዘሮ ቅድስት ወርቅሸት ግን ከነሱ የተለየ ሀሳብ አንስተዋል።

''ጥጥ እንዴት እንደሚባዘትና እንደሚፈተል ልጆቼ እንዲያውቁ የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው'' የሚሉት ወይዘሮ ቅድስት ይህም ልጆቻቸው ባህላቸውን እንዲያውቁና ለሌሎችም እንዲያሳውቁ ያደርጋል ብለዋል።

የአገር ባህል ልብሶችን ለእርሳቸውም ለልጆቻቸውም የሚያሰሩት ራሳቸው በሚፈትሉት ጥጥ መሆኑንም ነው የሚናገሩት።

በኢትዮጵያ በከተሞች አካባቢ ጥጥ መፍተልን የመሳሰሉት የቆዩ ባህላዊ የእደ-ጥበብ ስራዎች እየተረሱ መምጣታቸውን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም