ወጣቶች በጥምቀት በዓል የሚሰጡት የማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎ ጨምሯል

410

አዲስ አበባ  ጥር 11/2011 ወጣቶች በጥምቀት ከተራ በዓል በጽዳት፣ የበዓሉን ታዳሚዎች በማስተናበርና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የሚሰጡት የማህበራዊ አገልግሎት ሚና እየጨመረ መጥቷል።

የጥምቀት በዓል አከባበር አካል የሆነው ከተራ በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ዘንድ ዛሬ በድምቀት ተክብሯል።

በዚህ በዓል አከባበር የወጣቶች ተሳትፎ ከቀደመው ጊዜ መጨመሩን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣቶች ገልፀዋል።

ላለፉት 11 ዓመታት በጥምቀት በዓል ማህበራዊ አገልግሎት የሰጠው ወጣት ቢንያም አሰፋ ከስድስት ኪሎ አካባቢ ወጣቶች ጋር በመሆን በየዓመቱ ከሚያከናውነው መንፈሳዊ ተሳትፎ ባሻገር የማህበራዊ አገልግሎት ተሳትፎው እንደሚያስደስተው ይናገራል።

የአካባቢው ወጣቶች በማህበር በመሆንና አንድ አይነት ቲሸርት በመልበስ ማህበራዊ አገልግሎት ይሰጣሉ።

ወጣቶቹ በስድስት ኪሎ ወደ ጃንሜዳ የሚልፉ ታቦታትን በቅብብሎሽ በቀይ ምንጣፍ በመሸኘትና በመመለስ ያስተናግዳሉ፣ ጎዳና ያፀዳሉ፣ ያስተባብራሉ።

ቢንያም ባለበት የወጣቶች ማህበር ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊም ወጣቶችም በመኖራቸው በፍቅርና በአንድነት በዓሉን እያከበሩና ማህበራዊ አገልግሎት እየሰጡ እንደሆነ ገልጿል።

ወጣት በክረሮያል ኃይለእየሱስ በበኩሉ የአካባቢው ወጣቶች በየዓመቱ የበዓሉን ታዳሚ በማስተናበርና የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንደሚሰሩ ተናግሯል።

ታቦት የሚያልፍባቸውን ጎዳናዎች በማጽዳትና በማስዋብ ተግባር ላለፉት 15 ዓመታት መሳተፉን ገልጾ በዘንድሮው የጥምቀት ከተራ በዓል የወጣቶች ተሳትፎ መጨመሩን ገልጿል።

ከኢሉባቦር አካባቢ የመጣው ወጣት ግርማ ሲሳይም የጥምቀትን በዓል በአዲስ አበባ ሲያከብር ለሁለተኛው ጊዜ መሆኑን ገልጾ የወጣቶቹ ተግባር በእጅጉ እንዳስደሰተው ነው የተናገረው።

ወጣቶች በዓሉ ኃይማኖታዊ ይዘቱንና ተውፊቱን ጠብቆ እንዲቀጥል እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴ በማድነቅ ማህበራዊ አገልግሎታቸው ወደ ክልሎችም መስፋትና መጠናከር እንዳለበት አስተያየቱን አክሏል።