በሶማሌና በአፋር ክልሎች መካከል የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው....አቶ አደም ፋራህ

65

ደሬዳዋ ጥር 10/2011 በሶማሌና በአፋር ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አደም ፋራህ አስታወቁ።       

በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን ጠንካራ ትስስር ለመመለስ ቀደም ሲል ከፌደራል መንግስት፣ ከሁለቱ ክልሎችና ከፀጥታው ዘርፍ የተውጣጡ አካላት ያሉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ ሥራ ገብቶ ነበር።

በዚህም በአፋርና በሶማሌ ክልል መካከል የሚገኙ ሁንዱፎ፣ አይዳይቱ፣ ገርበኢሤ ቀበሌዎች በአፋር ክልል እንዲተዳደሩ ከተወሰኑ ዓመታት መቆጠሩን  አቶ አደም አስታውሰዋል።  

ይሁንና በአሁኑ ወቅት የታየውን ሀገራዊ ለውጥ ተከትሎ ቀበሌዎቹ ወደ ሶማሌ ክልል እንዲካለሉ የሚፈልጉ አካላት ካነሱት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተከሰተ ግጭት በዜጎች ላይ የሞት፣ የመቁሰልና የመፈናቀል ጉዳት ደርሷል።

በሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፋ ሙሐሙድ የተመራ የልዑካን ቡድን በችግሩ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸው በድል ጮራ ሆስፒታል በህክምና ላይ የሚገኙ ሰዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላም እስከ እኩለ ሌሊት ከኢሳ ባህላዊ መሪ ዑጋዝ፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሴቶችና ወጣቶች ተወካዮች ጋር በመወያየት ሁሉም ለዘላቂ ሰላምና አንድነት እንዲሰራ የጋራ መግባባት ላይ መደረሱን ነው የጠቆሙት።

የደረሰውን ጥፋት በማውገዝና የፌደራል መንግስት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያመጣ ለመጠየቅ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ በሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን በሚገኙ 10 ከተሞችነዋሪዎችህዝባዊ ሰልፍ ማድረጋቸውንም አቶ አደም ገልጸዋል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በተፈጠረው ግጭት እየታየ ያለው ጥፋት በፍጥነት እንዲቆም የፌደራል መንግስት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ ሰልፈኞቹ መጠየቃቸውንም ተናግረዋል።

ጅቡቲን ከድሬዳዋ የሚያገናኘው ዋና የአስፋልት መንገድ በሰልፈኞች ተዘግቶ እንደነበረም አመልክተዋል።

አቶ አደም እንዳሉት ችግሩን ለመፍታት ከሁለቱ ክልሎችና ከፌደራል መንግስት አስቸኳይ ኮሚቴ በማቋቋም ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ዳግም ወደሥራ ተገብቷል።

ድህነትና ኋላቀርነት፣ ጥቅማችን ይነካል የሚሉ አመራሮችና ኮትሮባንዲስቶች እንዲሁም ሀገራዊ ለውጡ ያልተዋጠላቸው አካላት ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መጋጨት ዋነኛ መንስኤዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

"እነዚህን አካላት በተቀናጀ መንገድ በመከላከል ሀገራዊ ለውጡን ማስቀጠልና ሰላምን ለማስጠበቅ በጋራ መስራት ይገባል" ብለዋል፡፡

በሲቲ ዞን ሽንሌ ወረዳ የሀገር ሽማግሌ የሆኑትና በሰልፉ ላይ የተሳተፉትሐጂ ሙሳ ሚጋድ" የአፋር ልዩ ፖሊስ በንጹሀን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ግድያ እናወግዛለን" ሲሉ ተናግረዋል።

" የፌደራል መንግስት ሰዎች እየሞቱ ዝም ብሎ መመልከት የለበትም " በማለትም መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

"የክልሉ መንግስትና የሀገር ሽማግሌዎች የሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሌላው በሰልፉ ላይ የታደመው ወጣት ሀሰን ኢስማኤል በበኩሉ አጥፊዎች ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የፌደራል መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቋል፡፡

የኢዜአ ሪፖርተር ባደረገው ቅኝት ከትናንት በስቲያ ተዘግቶ የነበረውና ጅቡቲን ከድሬዳዋና ከሲቲ ዞን የሚያገናኘው የአስፋልት መንገድ በትናንትናው ዕለት ሙሉ በሙሉ መከፈቱን አረጋግጧል፡፡

በሲቲ ዞን የአይሻ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኑር ሐሰን ለኢዜአ በስልክ እንደገለጹት ትናንት መንገዱ ሙሉ በሙሉ ተከፍቶ ተሽከርካሪዎች ወደ ድሬዳዋና ጅቡቲ በመመላስ ጀምረዋል፡፡

ነዋሪውና የፀጥታ አካላት ለመንገዱ አስተማማኝ ጥበቃ በማድረግ ላይ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በትናንትናው ዕለት ወደ ጅቡቲ ጉዞ የጀመሩት አቶ ታደለ ገረመው የተባሉ አሽከርካሪ በበኩላቸው መንገዱ በመዘጋቱ ድሬዳዋ ለማደር መገደዳቸውንና በዚህም የያዙት የግብርና ምርት ውጤት ላይ ብልሽት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም