ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ለሰላማዊ የትምህርት ስራ መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

85

ድሬዳዋ ጥር 10/2011 የሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈንና የመማር ማስተማሩ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን በሚከናወኑ ተግባራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቀረቡ፡፡

36ኛው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት ጉባኤ ዛሬ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል፡፡

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ  በጉባኤው መክፈቻ  ባስተላለፉት መልዕክት በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች   ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተ ቋማት ተማሪዎች ህብረት ከልብ በመነሳትና በማስተዋል በመስራት ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡

ተማሪዎች ከብሔር ፣ከኃይማኖት፣ ከጎሳ ክፍፍል እራሳቸውን በማራቅ ሀገራዊ ስብዕና በመላበስ ለሰላም መሳካት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 በዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩ ሥራ ስኬታማ ለማድረግ የጀመሩትን ጥረት ማጠናከር ይገባል ያሉት ዶክተር ያሬድ የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ምሳሌ በሚሆን በሰለጠነ ውይይት መፍታት እንደሚገባቸው  ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ህብረት ፕሬዘዳንት ተማሪ ይድነቃቸው አየለ በበኩሉ ሀገርን ለመለወጥና ቀጣይ ዘመንን የተደላደለ ለማድረግ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት ግንባር ቀደም  በመሆን ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ተናግሯል፡፡

" ሰላማዊ የመማር ማስተማር ተግባር እንዲሳካ ትልቁ ኃላፊነት የኛ ነው ፤ የተማሪዎችን ውሎና አዳር የምናውቅ እኛ ነን፤ ስለዚህ የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን ተወያይተን ለመፍታት ጠንክረን እንሰራለን" ብሏል፡፡

ተማሪ ይድነቃቸው  በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን  በሚደረገው ጥረት እንደሀገር ተቀናጅተው ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልጿል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ስነስርዓት የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ወንድወሰን መኮንን በሰላም እሴት ግንባታ፣ በግጭት መከላከልና አፈታት ላይ ፅሁፍ አቅርበው ጉባኤተኞቹ እየተወያዩበት ይገኛል፡፡

"ሰላም ቅድመ ሁኔታ የለውም " በሚል መሪ ሃሳብ በተጀመረውና ለሶስት ቀናት በሚቆየው ጉባኤ  ከ46 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ የተማሪዎች ህብረት አመራሮች እየተሳተፉ ነው፡፡

ተሳታፊዎቹ በሀገር አቀፉ የተማሪዎች ህብረት መሪ እቅድና በየዩኒቨርሲቲው ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ ተወያይተው መፍትሄ እንደሚያስቀምጡና በተጓደሉ  የህብረቱ አመራሮች ምትክ ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም