የኤሬር ቂሌ የውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

1389

ሀረር ጥር 10/2011 በሐረሪ ክልል ለወራት ተስተጓጉሎ የቆየው የኤሬር ቂሌ የውሃ ፕሮጀክት አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

ፕሮጀክቱ  ከ280 ሚሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ ተገንብቶ ከሐምሌ 2009 ዓ.ም.  አገልግሎት መስጠት ጀምሮ ነበር።

የአካባቢው ማህበረሰብ በሚያነሳው የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ፍትሃዊ ያልሆነ የካሳ ክፍያ  ጥያቄ ምላሽ መስጠት ባለመቻሉ ባለፉት  ወራት ፕሮጀክቱ አገልግሎት ተቋርጦ ቆይቷል።

በዚህም በተለይ በፕሮጀክቱ አቅራቢያ የሚገኙ ከ25ሺ በላይ ነዋሪዎች የችግሩ ተጋላጭ በመሆን በተደጋጋሚ  ቅሬታቸውን ሲቀርቡ እንደነበር ኢዜአ በተከታታይ ዘግቧል።

የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ እንደገለጹት  ተቋርጦ የነበረው የኤረር ቂሌ የውሃ አገልግሎት ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ችግሩ ተፈትቶ ስራ ጀምሯል።

ከትናንት ምሽት ጀምሮ በተለይ ለወራት የችግሩ ሰለባ ሆነው ለከረሙት ቀበሌ 15 እና 16 ነዋሪዎች አቅርቦቱን በቅድሚያ እንያገኙ ተደርጓል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት በአርሶ አደሩ አካባቢ የሚገኙ የውሃ ታንከሮችን የመሙላትና ሌሎች ተጓዳኝ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፤ይህም የክልሉ ነዋሪ በተደጋጋሚ  ይጠይቅ የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት  ችግር ለመፍታት ያግዛል።

የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ዩስፍ በበኩላቸው የኤረር ወረዳ ነዋሪዎች የመልካም አስተዳደርና የካሳ ጥያቄ ምላሽ አልተሰጠንም በሚል ቅሬታ እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡

ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ውይይት ተደርጎ የመልካም አስተዳደር ችግር የነበረው የውሃ አገልግሎቱ መፍትሄ ማግኘት እንደጀመረ አመልክተዋል፡፡

ከልማቱ አለመጠቀምና በወቅቱ የተደረገው የካሳ ክፍያ ፍትሃዊነት የጎደለው እንደነበር አርሶ አደሮቹ ያነሱት ቅሬታ ለመፍታት ከአርሶ አደሩና ከክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የተወጣጡ ተወካዮችን ያቀፈ   ኮሚቴ ተዋቅሮ ጉዳዩን ዳግም የመመልከት ስራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ይህም አመራሩ ቀደም ሲል የህብረተሰቡን ጥያቄ  በአጭር ጊዜ ለመፍታት ያቀደው ስራ እንደነበር ጠቁመው “በቀጣይም ነዋሪው የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በተገቢው የመፍታቱ  ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል “ብለዋል።

ከአካባቢው አርሶ አደሮች መካከል  አቶ ኡስማኤል መሀመድ እንደተናገሩት  ከውሃውም ሆነ ከሌሎች የልማት ስራ ገበሬው ተጠቃሚ ባለመሆኑና  ጥያቄውን ተመልክቶ ምላሽ የሚሰጥ አመራር ባለማግኘታቸው ችግር ተፈጥሮ ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን  አመራሩ ጥያቄውን እንደሚመልስላቸው መግባባት ላይ መድረሳቸውን  ገልጸዋል፡፡

መወያየቱ  ነዋሪውን ለችግር የሚዳርጉ ተግዳሮቶችን መፍታት ስለሚያስችል እንዲህ ዓይነቱ አሰራር መጎልበት እንደሚገባው ያመለከቱት ደግሞ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ ሔለን ሳሙኤል ናቸው።