በጋምቤላ ክልል የሐሩራማ በሽታዎች መከለከያ መድኃኒት በዘመቻ እየተሰጠ ነው

64

ጋምቤላ ጥር 10/2011 በጋምቤላ የሐሩራማ በሽታዎች መከላከያ መድኃኒት በዘመቻ መልክ እየተሰጠ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የጤና ማበልጸግና በሽታ መከላከል ዋና የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሪያንግ ፖች ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የሐሩራማ በሽታዎች መከላከያ መድኃኒት ከትናንት ጀምሮ በዘመቻ መልክ እየተሰጠ ነው፡፡

መድኃኒቱ እየተሰጠ ያለው በክልሉ የህብረተሰቡ የጤና ችግሮች ተብለው ከተለዩት ስድስት የሐሩራማ በሽታዎች ለአራቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መድኃኒቶቹ እየተሰጡ ያለው ለዝሆኔ፣ ለአንጀት ጥገኛ ትላትል፣ ለቢልሃርዝያና ለኦንኮሰርኪያሲስ (የማሳከክ) በሽታዎች መሆኑን ተናግረዋል።

በዘመቻው በክልሉ 8 ወረዳዎች በሚገኙ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በላይ ለሆኑ ከ277 ሺህ የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የኦንኮሰርኪያሲስና የዝሆኔ በሽታ መከላከያና የህክምና በመድኃኒት እየተሰጠ ነው።

በክልሉ በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች ከ5 እስከ 14 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ለሚገኙ 138 ሺህ ህናፃትና ወጣቶች የአንጀት ጥገኛ ትላትል መድኃኒት እየተሰጠ መሆኑንም አቶ ሪያንግ አመልክተዋል፡፡

እንደ ስራ ሂደቱ  ገለጻ ከ15 እስከ 19 የዕድሜ ክልል ለሚገኙት 57 ሺህ ታዳጊ ህፃናትና ወጣቶች የብልሃርዝያ በሽታ መከላከያ መድኃኒቶች በመሰጠት ላይ ናቸው።

አቶ ሪያንግ እንዳሉት የኦንኮሰርኪያሲስ (የማሳከክ) በሽታ መከላከያ መድኃኒት ቁመታቸው አንድ ሜትር ከ10 ሲንቲ ሜትር በታች ለሆኑ ህፃናት፣ በፀና ለታመሙ ሰዎች፣ ለነፍሰጡርና ለአራስ እናቶች አይሰጥም።

የኦንኮሰርኪያሲስ በሽታ በጥቁር ዝንብ ንክሻ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን የዝሆኔ በሽታም በወባ ትንኝ ንክሻ የሚተላለፍ መሆኑን አስረድተዋል

የኦንኮሰርኪያሲስ  በሽታ ሰውነትን በከፈተኛ ሁኔታ የሚያሳክክ፣ ቆዳን የሚያዥጎረጉርና ለዓይነ ስውርነት የሚዳርግ ሲሆን የዝሆኔ በሽታም እግርን፣ በወንድ የዘር መራቢ ፌሬዎችና በሴቶች ጡት ላይ የእብጠት ችግር እንደሚያስከትል አብራርተዋል፡፡

ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የተቀናጀ የሐሩራማ በሽታዎች መከላከያ መድኃኒት እደላ ዘመቻ ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ጨምሮ ሁለት ሺህ የሚጠጉ በጎ ፍቃደኞች መሰማራታቸውን የሥራ ሂደት ኃላፊው መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም