የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊ ትውፊቱን ባይለቅም ባህላዊ ይዘቱ ከድሮው እየተለየ መጥቷል

135

አዲስ አበባ ጥር 10/2011 የጥምቀት በዓል አከባበር ኃይማኖታዊ ትውፊቱን ባይለቅም ባህላዊ አከባበሩ ከድሮው  የተለየ ቅርጽ እየያዘ መምጣቱን አባቶች ተናገሩ፡፡

የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ  ክዋኔው ባለፈ ባሕላዊ እሴቶች የሚንጸባረቁበት ትልቅ የአደባባይና የአንድነት በዓል ነው፡

በቀደመው ጊዜ ታቦታቱ በከተራ ዕለት ከመንበራቸው ተነስተው ወደ ማደሪያቸው ውሃማ ስፍራ ሲሄዱ በዝማሬና በሆታ በማጀብ ከማድረስ ጀምሮ በሚኖራቸው አዳርም በተለይ ወጣቶች የተለያዩ ባሕላዊ ጨዋታዎችን ያከናውኑ እንደነበር አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አባቶች ተናግረዋል፡፡

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ሙላቱ ተዋበ

"የድሮው እንዴት መሰለህ ድባቡ በጨዋታ፣ በዘፈን በእልልታ ምናምን ልጆች ወጣቶች በየቋንቋቸው እየዘፈኑ እያጨበጨቡ ቤተክርስቲያን ያስገባሉ።"

"የጥምቀት በዓል በእኛ ጊዜ በእውነቱ ወንዱም ሴቱም ሽማግሌ አረጋዊም ህጻናትም ነጭ በነጭ ልብሱን ለብሶ ያማረ ልብስ ለብሶ ደምቆ አምሮ ታቦተ-ህጉን ከመንበረ ጸባኦቱ ጥር 10 ታቦቱን አጅቦ በካህናት ታጅቦ ወደ ጥምቀተ ባህሩ ይወርዳል። የሚሉት ደግሞ ሊቀ መዘምር አማረ ኢሳያስ ናቸው፡፤

ከዚህ ሌላ አማኙ ያለውን ነጭ ልብስ በማጠብ አምሮና ደምቆ በዓሉን ያከብር እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

በገጠሩ አካባቢ ፈረስ ጉግስን ጨምሮ ወጣቶች ልጃገረዶችን የሚያጩበት ባህላዊ ሥርዓት ለበዓሉ ተጨማሪ ድባብ የሚፈጥር እንደነበር ያስረዳሉ፡፡

በተለይ በሎሚ ውርወራ ለመተጫጨት የሚደረገው እንቅስቃሴ የተለየና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ እንደነበር በማንሳት ሂደቱን እንዲህ ይገልጹታል፡፡  

አቶ ኃይለመስቀል አይጨነቁ

"ሎሚ ሴቷ ናት ለወንዱ የምትሰጠው ከዚያም በኋላ እሱ መልሶ ይወረውራል። ከዚያ በኋላ ይተጫጫሉ ፈቃደኝነት በዓይን ነው የሚገላለጹት እዚያ ማዶ ያ እዚያ ማዶ ሆነው የሚገላለጹት በዓይን ነው" 

አቶ ሙላቱ ተዋበ በበኩላቸው "በሩቁ ያያታል ሎሚ ይወረውርላታል፤ እሷ ፈቃደኛ ከሆነች ትቀበለዋለች ፈቃደኛ ካልሆነች ፊቷን ተሸፋፍና እፍረት አለ ያፍራሉ የድሮ ሰዎች ግልጽ እንዳሁኑ እንትን አይደሉም በግድ ነው በጓደኛ ተባብላ ምን ተብላ ነው"

በመተጫጨት ሂደት ተዋደው የሚዘልቁ እንዳሉ ሁሉ የማይቀጥሉ መኖራቸውንም እኚሁ አባቶች  ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው የጥምቀት በዓል አከባበር ግን ምንም እንኳ ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ባይለቅም ቀድሞ በዓሉን የሚያደምቁ ባህላዊ ክዋኔዎችን እያጣ መሄዱን ነው አዛውንቶቹ የሚገልጹት።

አሁን ላይ ጭፈራው በአብዛኛው ወደ ዝማሬ የተቀየረ ቢሆንም  ከቀድሞው በተሻለ አዲስ የበዓል አከባበርና አዲስ ድምቀት ይዞ መጥቷል ብለዋል።

በተለይ ወጣቱ ለሃይማኖቱ ያለው አቋም እየተጠናከረ የመጣበት መሆኑን በመግለጽ ወጣቱ ሊመሰገን እንደሚገባም አውስተዋል፡፡

በመንበረ ፓትርያርክ የትንሳኤ ዘ-ጉባኤ ማተሚያ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ የቀድሞውና የአሁኑ በዓል አከባበር ሃይማኖታዊ መሰረቱን ለቆ የማያውቅ እንደሆነና ከአከባበር አንጻር ግን ዘመኑን ተከትሎ የተለወጠ መኖሩን ይናገራሉ።

ቀድሞ በዓሉ ካህናት ያሬዳዊ ዜማ እናቶችና አባቶች ደግሞ በራሳቸው ቋንቋ ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑበት እንደነበር በምሳሌ በማስታወስ፡፡

የአሁኑ ትውልድ ለበዓሉ ያለው ፍቅር አለመቀነሱን የሚናገሩት ንቡረ እድ የሚከናወኑ ተግባራት ሁሉ ግን በመታዘዝ ላይ መመስረትና ማከናወን እንዳለባቸው ይመክራሉ፡፡

ታቦታቱን ስናጅብ በንጽህና ራስን ከክፉ ነገር ጠብቆ መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የእድሜ ባለጸጋ አባቶች በዓሉ የሰላምና የፍቅር የአንድነት እንዲሆንም ተመኝተዋል፡፡  

በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በተደረገው ጥረትም ዩኔስኮ ለሚቀጥለው ዓመት ቀጠሮ እንደያዘለት ሰምተናል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም