ካሣና ተለዋጭ ቦታ ባለመመቻቸቱ መቸገራቸውን በአርባ ምንጭ ሆስፒታል ግንባታ የልማት ተነሽዎች ገለጹ

65

የአርባምንጭ ጥር 10/2011 የንብረት ካሣና ተለዋጭ ቦታ ባለመመቻቸቱ መቸገራቸውን በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ምክንያት ከይዞታቸው የሚነሱ ግለሰቦች ገለጹ፡፡

ከተነሺዎች መካከል በሼቻ ክፍለ ከተማ የበሬ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አንተነህ ጌታቸው ለኢዜአ እንዳሉት በሆስፒታሉ ግንባታ ምክንያት ከይዞታቸው ሲነሱ ተመጣጣኝ የካሣ ክፍያና ቦታ እንደሚያገኙ ከተነገራቸው ሶስት ዓመታት አልፎታል፡፡

በዚህም ምክንያት ማንኛውንም ልማት በይዞታቸው ማከናወን እንዳይችሉ ታግደው  ህይወታቸው እንዳይረጋጋ በማድረጉ መንግስት ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ፡፡

ሌላዋ የልማት ተነሽ ወይዘሮ ቤዛ ታደሰ በበኩላቸው  መንግስት ለብዙኃኑ ህዝብ ልማት ሲል ከይዞታቸው እንዲነሱ መደረጉን እንደማይቃወሙ ገልጸው በተገባው ቃል መሰረት ተመጣጣኝ ክፍያ ባለማግኘታቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

ተመጣጣኝ ቦታና ካሣ እንዲከፈላቸው  የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደርና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን በተደጋጋሚ ጠይቀው  ቃል ከመግባት ባለፈ ተፈጻሚ ባለመሆኑ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን አስረድተዋል፡፡

አዲስ ልማት እንዳያከናውኑ በመታገዳቸው መኖሪያ ቤታቸውንም ሆነ የመኖሪያ ቤት አጥራቸውን ማደስ እንዳልቻሉ የተናገሩት ደግሞ  የልማት  ዋና ሳጂን ተስፋዬ ቱርካ የተባሉ የልማት ተነሽ ናቸው፡፡ 

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ታሪኳ ወልደመድህን ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ተነሺ ግለሰቦች ማግኘት ከሚገባቸው ጥቅም አንጻር ያነሱት ጥያቄ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

ለተነሺዎች የንብረት ካሳም ሆነ ከቀበሌ ቤት ለሚወጡ ግለሰቦች ለሚገነባው ግንባታ በቂ በጀት መመደቡን ገልጸው ጠቅሰው ቦታ የማመቻቸቱ ሥራ ግን የከተማ አስተዳደሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ማዶ መንገሻ በበኩላቸው  ለልማት ተነሽዎች የቀበሌ ቤቶችን ለመስጠት መወሰኑን ገልጸው የዘገየው በነበረው የጸጥታ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከሪፌራል ሆስፒታል ግንባታ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ግለሰቦች ጥያቄ በያዝነው የበጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ ምላሽ እንደሚያገኝም አስታውቀዋል፡፡

ተነሺዎቹ  26 ግለሰቦች እንደሆነ ተመልክቷል፡፡

በ875 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተገነባ ያለው የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ከመጋቢት 9/2007 ዓ.ም. ጀምሮ ግንባታው እየተከናወነ ሲሆን አፈጻጸሙ 70 በመቶ መድረሱ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም