የባህል አልባሳት ገበያው መቀዛቀዝ ታይቶበታል

136

ጥር 10/2011 የሀገር ባህል አልባሳት ለአለባበስ አመቺ በሆነ ዲዛይንና አማራጭ ተሰርተው እየቀረቡ ቢሆኑም ዋጋቸው እየጨመረ በመምጣቱ ለመግዛት አልቻልንም ሲሉ የባህል ልብስ ሸማቾች ተናገሩ።   

በሌላ በኩል ዋጋቸው ቢወደድም ሀገር በቀል ባህላዊ አልባሳትን ለመጠበቅ ዋጋ ልንከፍል ይገባናል ይላሉ በሽሮ ሜዳ የባህል ልብስ ሲገዙ ያገኘናቸው ሸማቾች።

የኢዜአ ሪፖርተር በሽሮሜዳ አካባቢ የባህል አልባሳት ገበያ ተዘዋውራ ባደረገችው ቅኝት የባህል አልባሳት  ገበያው ከሌላው ጊዜ ባልተለመደ ሁኔታ መቀዛቀዝ ይታይበታል፡፡

በአካባቢው የባህል ልብስ ሲገዙ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ኤልሳ በላይ እንደገለፁት የሀገር ባህል አልባሳት ከበዓል በዘለለ ለተለያዩ ፕሮግራሞች በሚመች መልኩ እየቀረቡ ነው።

“ምንም እንኳ የአገር ባህል ልብሱ ዋጋው ቢወደድም የማንነታችን መገለጫ፣ ገፅታችን የምንገነባበት የአገራችን ሸማኔዎች የጥረት ውጤትና የእጃቸው ጥበብ በመሆኑ ባህሉን ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቅብናል” ነው ያሉት፡፡

የባህል ውጤት የሆኑ ልብሶች በማሽን ተገልብጦ ሀገር ውስጥ በተመሳሳይ እየገቡ ያሉ ምርቶች የአእምሮ ስርቆት እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ኤልሳ መፍትሔ ሊበጅበት ይገባልም ይላሉ። 

ገበያው ላይ ብዙ የሀገር ባህል አልባሳት አማራጭ ቢኖርም ዋጋቸው ግን ˝አይቀመስም˝ያሉት የባህል ልብስ ሲገዙ ያገኘናቸው አቶ አዲሱ አረጋ፤ ዋጋውን ከፍ በማድረግ እየተጠቀመ ያለው ግን ሸማኔው ሳይሆን ነጋዴው ነው የሚል እምነት አላቸው።

አቶ አዲሱ እንደተናገሩት በጥራት የተሻለ እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ተወዳዳሪ የሆኑ የባህል አልባሳት ማምረት እየተቻለ የማስተዋወቅ ዓቅማችን ዝቅተኛ በመሆኑ ተመሳስለው በመግባት ላይ ያሉ ምርቶች ገበያውን  እየተቆጣጠሩት ነው። 

በአገር ውስጥ ጥሬ እቃ የሚመረተው የባህል ልብስ ዋጋው ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ የሚኖሩበትን የአየር ሁኔታ ያላገናዘበ ምርት ቢሆንም ተመሳስሎ ከውጭ የሚገባውን ምርት ለመጠቀም መገደዳቸውን የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አልማዝ በዛብህ ናቸው፡፡

በሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳት ነጋዴ ወይዘሮ ማናለ ቢረዳኝ  በሰጡት አስተያየት የበአል ገበያው ካለፉት ዓመታት በተለየ ሁኔታ መቀዛቀዝ የታየበት መሆኑን ተናግረው ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያነሱት ደግሞ  ከውጭ ተመሳስለው የሚገቡ ዋጋቸው ዝቅተኛ በመሆኑና የጥሬ እቃ መወደድ ገበያው ላይ ተጽኖ ማሳደሩን ነው።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህልና ኢንዳስትሪ ልማትና ትብብር ዳይሬክተር አቶ ይስማአ ፅጌ እንዳሉት በሁሉም የመሸጫ ቦታዎች ተመሳሳይ ችግሮች መታየታቸውን ገልፀው ተቋሙ ይሄን የመከልከል መብትም አሰራርም እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት የሀገር ውስጥ ምርቶች ተወዳዳሪና ተመራጭ እንዲሆኑ  መስራት ያስፈልጋል።

አቶ ይስማአ እንዳሉት በአምራቾችና አቅራቢዎች በኩል የባህል አልባሳቱ ተጠቃሚዎች በፈለጉት ጊዜ ያለማቅረብ፤ የምርት ጥራት ማነስ፣ በብዛት ያለማምረትና ለማምረት ከሚወስደው ጊዜ አኳያም የዋጋ መወደድ ከውጭ እንደሚገቡት ምርቶች በቀላሉና በሚፈለገው መጠን በማንኛውም ሱቅ ስለማይገኙ ነው። 

ችግሮቹን ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በቴክኒክና ሙያ ስልጠናዎች በመታገዝ የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ማገዝ የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመሩንም አቶ ይስማአ ገልፀዋል። 

“ይህ ችግር በኛ አገር ባህል ልብስ ብቻ የተገደበ አይደለም” የሚሉት ዳይሬክተሩ ቱሪስቶች የሌሎች ሀገራት ምርቶችንም ፎቶ አንስተው ወስደው አመሳስሎ በማምረት ለገበያ ስለሚያቀርቡ በርካታ የአፍሪካና ኤስያ ሃገራትም እየተቸገሩ እንደሆነ ተናግረዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም