በደብረ ብርሃን ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የኤሌክትሪክ ሰብስቴሽን ስራ ጀመረ

63

ደብረብርሃን ጥር 10/2011 በደብረ ብርሃን ከተማ በ60 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የኤሌክትሪክ ሃይል ማከፋፈያ ሰብ ስቴሽን 110 ሜጋ ዋት ሃይል በማቅረብ ስራ ጀመረ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አብርሃም በላይ ትላንት የሰብ ስቴሽኑን ስራ ባስጀመሩበት ወቅት እንደገለፁት በሃገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅፋት የሆነውን የሃይል አቅርቦት እጥረት ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሰራ ይገኛል።

"ይህ ሰብ ስቴሽን በአካባቢው ከቱለፋ እስከ ደብረብርሃን ከተማ ድረስ ያለው የእንዱስትሪ ዞን የሚያስፈልገውን የሃይል ጥረት ለመፍታት ያግዛል" ያሉት ዶክተር አብርሃም ቀደም ሲል በባለሀብቶችና በነዋሪዎች ይነሱ የነበረውን ቅሬታ እንደሚመልስም ጠቁመዋል።

በአካባቢው ካለው የኢቨስትመንት ፍሰት ጋር ተጣጥሞ ሊሄድ የሚችል ተጨማሪ ሰብ ስቴሽን ለመገንባት ዝግጅትም እየተካሄደ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተፈራ ወንድምአገኘሁ በበኩላቸው እንደገለጹት ዞኑ በኢንቨስትመንት መዳረሻነት ተመራጭ ቢሆንም በሃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ሲቸገሩ ቆይተዋል።

“የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦቱ መሻሻሉም ግንባታቸዉን አጠናቀዉ በመብራት ሃይል ባለመኖር ምክንያት ወደ ማምረት መግባት ያልቻሉ ኢንዱስትሪዎችን መሰረታዊ ችግር የፈታ ነው”ብለዋል።

በቀጣይም አዳዲስ ባለሃብቶችን ወደ አካባቢው በመሳብ በእንስሳት ሀብት፣ በኢንዱስትሪና በማእድን ልማት እንዲሁም በሆቴልና ቱሪዘም ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደብረበርሃን ዲስትሪክት ሃላፊ አቶ ምንተስኖት ተስፋየ በበኩላቸው በነዋሪዎችና በባለሀብቶች ይነሱ የነበሩትን ጥያቄዎች ለመመለስ ከሰብ እስቴሽኑ ሀይል በማውጣት ለማሰራጨት የመስመር ዝርጋታ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

“ተጨማሪ የሃይል አቅርቦቱ ለደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎችና በአካባቢው ለተገነቡ ኢንዱስትሪዎች ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲደርስ ይደረጋልም”ብለዋል።

የዞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ መምሪያ የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ቡድን መሪ አቶ ዮሐንስ ሽፈራው በበኩላቸው በአካበቢው ካሉ 50 አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል 11ዱ በመብራት ሃይል አቅርቦት እጥረት ምክንያት በጀኔረተርና በፈረቃ እንዲሰሩ ተደርጓል።

እንዲሁም ስድስት ታላላቅ የማምረቻ ፋብሪካዎች በሃይል አቅርቦት ምክንያት ለረጅም ጊዜ ግንባታቸውን አጠናቀው ያለስራ ቆመው መቆየታቸውን አመልክተው በዚህም በባለሃብቶች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲቀርብ መቆየቱን አስረድተዋል።

“ቀደም ሲል ለአካባቢው ይቀርብ የነበረው 28 ሜጋ ዋት ብቻ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ተጨማሪ ሃይል መቅረቡ የባለሃብቶችንም ሆነ የነዋሪዎችን የረጅም ጊዜ ጥያቄ ይፈታል”ብለዋል።

የሃይል ማከፋፈያ ሰብ ስቴሽኑ ከመጋቢት 2009 ዓ.ም ጀምሮ በስምንት ሄክታር መሬት ላይ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል እንደተገነባም ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም