ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ

1268

በወንድማገኝ ሲሳይ (አዳማ ኢዜአ)

ጥምቀት ከከተራ እስከ ቃና ዘገሊላ በተከታታይ በከፍተኛ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው።ይህ ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ከሕዝቡ ባህል ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው በመሆኑ ከሃይማኖታዊ በአልነቱ ባሻገር ባሕላዊ ፋይዳው የጎላ ያደርገዋል።

በዓሉን ለመታደም በሀገር ውስጥ ካለው ሰፊ ማህበረሰብ ባለፈ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና መንፈሳዊ ተጓዦች ወደ ኢትዮጵያ ይተማሉ።

የሐይማኖት አባቶች ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር ፣ መታጠብ የሚሉ ትርጓሜዎችን ይሰጡታል፡፡

የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡ የከተራ እለት ጥር 10 ሲሆን  ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ ፣ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ።

ዲያቆን ፍቃዱ ደመረ የአዳማ ቅድስት ማርያም ካቴድራል ቤተክርስቲያን አገልጋይ ሲሆኑ የጥምቀት በዓል በማስመልከት ከሱ ጋር ጥቂት ቆይታ አድርጌ ነበር።

እንደ ዲያቆን ፍቃዱ ገለፃ በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሠረት ዓበይት በዓላት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡

ይህም በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጥመቁ ዮሐንስ ፤ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበትን ቅድስት ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ከዋዜማው ከጥር 10 ጀምሮ በደመቀ ሁኔታ ታከብራለች ይላል፡፡

ለእኛ አብነት ይሆነን ዘንድ፤ የእዳ ደብዳቤያችንን እንደ ገል ቀጥቅጦ እንደ ሰም አቅልጦ በደላችንን ይደመስስ ዘንድ ጌታ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቁን ይናገራል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይህንን መሠረት በማድረግ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚገኙ ታቦታት በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ በካህናትና ዲያቆናት እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቶች መዘምራንና ምዕመናን በዝማሬ በመታጀብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ታቦት ማደሪያ በማምራት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ በመሔድ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ማምራቱን ያበስራሉ ሲል ይገልፃል፡፡

መጸሀፍ ቅዱስ “ያን ጊዜም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ናዝሬት መጣ ዮሐንስም በዮርዳኖሰ ወንዝ አጠመቀው” እንዲል፡፡ /ማቴ.3፡1/ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን መስራቿን መድኅነ ዓለም ክርስቶስን ለዓለም የምትሰብክበት እንደሆነም እንዲሁ።

በተለይ ዓለም እንደሚሰጠው ያልሆነውን፣ የእግዚአብሔር ልጅነት፣ ሰላም፣ ፍቅርና ትሕትና ለዓለሙ ትሰብክበታለች ነው ያለው፡፡

ለሀገራችን በጎ ገጽታን በመፍጠር ረገድ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ጎብኚዎች ተደንቀው የሚያዩትና በመስተንግዶው የሚደመሙበት በመሆኑ ሃይማኖታዊ በዓሉን በልዩ ትኩረት እንደሚከበር ነው ዲያቀኑ ያስረዳው።

ለዚሁ ለጥምቀት በዓል የከተማውን ዝግጅት በተመለከተ በጥምቀተ ባህሩ አካባቢ ማለትም በአዳማ መስቀል አደባባይ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።

እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ የውሃ ቦቴዎችና ለምእመናንን ጠበል የሚያዳርሱ እስከ 50 ሜትር የሚረጭ የውኃ ማስተላለፍያም ተዘጋጅቶአል።

የአዳማ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ባለሙያ ዋና ሳጂን ወርቅነሽ ገልሜቻ በበኩላቸው በዓሉን ለማክበር የደህንነት ስጋት የለም ይላሉ።     

የጥምቀት በዓል ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም እንዲከበር የከተማው ፖሊስ መምሪያ በከተማዋ መውጫና መግቢያ በሮች ተገቢውን ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ይናገራሉ።

በተለይ ከአርሲ፣ሐረር፣ምንጃርና ወንጂ ወደ ከተማዋ በሚያስገቡና በሚያስወጡ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ፖሊስ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ከለህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ሰላምን ማረጋገጥ አዳጋች በመሆኑም ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆነ ጉዳይ ሲያጋጥመው ለፖሊስ አካል በመጠቆም ትብብር እንዲያሳይ ጠይቀዋል።

ወጣት ምህረት ዓለሙ በአዳማ ከተማ የገዳ ቀበሌ ነዋሪና የሰንበት ትምህርት ቤት አባል ነው።እሱ እንደሚለው ለጥምቀት በዓል አከባበር ቤተክርስቲያን ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ታቦታት በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲመለሱ ጉልህ ሚናዋን ትወጣለች፡፡

ለዚህ ስኬት በየአጥቢያው አካባቢ  የሚገኙ ወጣቶች ከክብረ በዓሉ ቀደም ብሎ በመሰብሰብ ለታቦታት ማረፊያዎች እንደሚያዘጋጁ በመጠቆም።

ወንጌልን የሚሰብኩ ባነሮችን፣ሰንደቅ ዓላማን በየአደባባዮች በመስቀል፣ የቤተክርስቲያናትን ቅጥርና አስፋልት በማጽዳት ፤ለታቦት ክብርን ለመስጠት ምንጣፎችን በማንጠፍ በዓሉን ለማድመቅ መዘጋጀታቸውን ገልጿል፡፡

ከዋዜማው ከከተራ ጀምሮ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ በክብር ወጥተው በህዝቡ እልልታ፣ ሽብሽባና በካህናቱ ውብ ያሬዳዊ ዜማ ወደ አዳማው መስቀል አደባባይ የሚተሙበት በመሆኑም በዓሉን በጉጉት እየጠበቀው ይገኛል።

ሌላኛው ወጣት አቤል አሰፋ የጥምቀት በዓል ሕዝበ ክርስቲያኑ በሰፊው የሚሳተፍበት በመሆኑ ልዩ ፍቅር እንዳለው ይናገራል።

በከተማዋ በተለይም በወጣቶች ዘንድ የጥምቀት በዓል አከባበር የራሱ ገፅታ እንዳለው የሚገልጸው አቤል በተለይ ወጣቱን ለጨዋታ የሚጋብዝና የሚስብ ትዕይንት መሆኑን አመልክቷል፡፡

የጥምቀት በዓል ሲከበር ዕለቱን ለማድመቅ ጭፈራና ድለቃው አይቀርም። በዚህ ቀን የልጅነት ጊዜያችንን፣የዓምናና ካቻምናውን አከባበር እንድናስታውስ የሚያደርገን መዘክርም አለው።

ያኔያኔ ወጣቱና ጎልማሳው የጥምቀት በአልን ለማክበርና ጭፈራቸውን ለማድመቅ ምርጫ ከሚያደርጓቸው መካከል የባህል ጫወታ ዋንኛው ነው።

ፉክክሩም ብዙ ጊዜ  ብሄርን፣ ሰፈርንና አካባቢን በለየ መልኩ ይጧጧፏል።ይህ ደግሞ ልዩ ደስታን ይሰጣል። 

ውብና ድንቅ የሆነውን ይህን ክብረ በዓል ለማክበርና ለማየት  አገር ተሻግረው የሚመጡ ቱሪስቶችን መመልከትም ሌላው የበዓሉ ነጸባራቅ ነው።

 በዚህ አጋጣሚ መልካም የጥምቀት በዓል እየተመኘው በሰላምና በጤና የዓመት ሰው ይበለን እላለሁ።