በመንግስትና የግል አጋርነት የሚተገበሩ ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለጨረታ ሊቀርቡ ነው

80

አዲስ አበባ  ጥር9/2011 በኢትዮጵያ መንግስትና የግል አጋርነት የሚተገበሩ ስድስት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናታቸው ተጠናቆ ለጨረታ ሊቀርቡ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚንስትር ዴኤታው ዶክተር ተሾመ ታፈሰ ጉዳዩን አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ ያቋቋመው ቦርድ በዘርፉ ከለያቸው 16 ፕሮጀክቶች ውስጥ አስራ ሶስቱ በኃይል አቅርቦት ሲሆኑ ሶስቱ የትራንስፖርት ፕሮጀክቶች እንደሆኑም ይታወቃል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በኃይል አቅርቦት ከተለዩ 13 ፕሮጀክቶች መካከል ስድስቱ የአዋጭነት ጥናታቸው ተለይቶ ወደ ጨረታ ሂደት የሚያስገባቸው ተግባራት እየተከናወነ ነው።

እነዚህ ፕሮጀክቶች 798 ሜጋ ዋት ኃይል የሚያመነጩ ሲሆን ለፕሮጀክቶቹ 795 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቶቹም በአራቱ የአገሪቷ ክልሎች በአፋር፣ ሶማሌ፣ ኦሮሚያና በትግራይ የሚተገበሩ ሲሆን ሙሉ ወጪውን የሚሸፍነው ጨረታውን የሚያሸንፈው የግል ባለሃብት መሆኑም ተናግረዋል።

በአፋርና በሶማሌ የሚተገበሩት ዲቼቶና ጋድ የተሰኙ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመንግስት ጋር ለሚሰራ የግል ባለሃብት ጨረታ የሚቀርብ ሲሆን ቀሪዎቹ በሂደት የሚከናወኑ መሆኑንም ተናግረዋል ዶክተር ተሾመ።

መንግስት በጉዳዩ ዙሪያ ትልቅ ትኩረት የሰጠና  የሌሎች አገሮችን ተሞክሮንም በስፋት መቃኘቱን አስታውሰው ለፕሮጀክቶቹ አፈፃፀም የህግና ተቋማዊ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

ፕሮጀክቶች ለህዝብ አስፈላጊና በመንግስት አቅም ለመተግበር ሰፊ የገንዘብ አቅም የሚጠይቁ በመሆናቸው አቅም ያላቸው የግል ባለሃብቶች ገብተው እንዲተገብሩት ፖሊሲ መውጣቱ ይታወቃል።

ባለፉት ስድስት ወራት እነዚህን ፕሮጀክቶች በበላይነት የሚቆጣጠርና በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የሚመራ እንዲሁም መንግስትን ወክሎ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ዘጠኝ አባላት ያሉት ቦርድ መቋቋሙም ይታወሳል።

የመንግስትና የግል ባለሃብቱን ያሳተፈበት ዋነኛ ዓላማም የህዝብ አገልግሎትን በፍጥነትና በጥራት ለማከናወንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት እንዲሁም እያደገ የመጣውን የህዝብ ፍላጎት ለመመለስ  ነው።

ፕሮጀክቶቹም የአገሪቱን ራዕይና የልማት ዕቅድ መሰረት አድርገው የሚከናወኑ በመሆናቸውና ውስብስብና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሹ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በፕሮጀክቱ ለመሳተፍ በርካታ የግል ባለሃብቶች ፍላጎት ማሳየታቸውንም አስታውቀዋል።

በትራንስፖርት ዘርፉ የአዳማ አዋሽ፣ አዋሽ ሚኤሶና የሚኤሶ ድሬደዋ መንገድ ከተያዙ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም