ለሀገር ሰላም አንድነታቸውን እንደሚያጠናክሩ የባሌ ጎባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ገለጹ

61

ጎባ ጥር 9/2011 በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍንና ሀገራዊ ለውጡ ከግብ እንዲደርስ አንድነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የባሌ ጎባና አካባቢዋ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ፡፡

ነዋሪዎቹ ይህንኑ ያሉት ዛሬ በጎባ ከተማ ባካሔዱት የሰላም ኮንፈረንስ ላይ ነው።

በሰላም ኮንፈረንሱ ከተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች መካከል ቆሞስ አባ ወልደሚካኤል እንደተናገሩት "በየአካባቢው የሰላም መደፍረስ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ አካላትን እንጂ የሰላም ወዳዱን ህብረተሰብ ፍላጎት አያንጸባርቅም" ብለዋል።

"በቀጣይም ህዝቡ በአካባቢው ሰላም ላይ እንዲያተኩርና በጥፋተኞች ሴራ እንዳይታለል ከማድረግ ጀምሮ አንድነቱን በማጠናከር የሃይማኖት አባትነት ሚናችንን እንወጣለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሼህ ካሚል አልይ በበኩላቸው “ ጎባ ለሌላው የሀገሪቱ ህዝብ የሰላም ምሳሌና የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የሚኖሩባት ከተማ ናት" ብለዋል፡፡

ይህን ሰላምና ህብረት የማይፈልጉና አገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃይሎች የህዝብን ሰላም እንዳያናጉ በጋራ መከላከል ለውጡን ከዳር ማድረስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ያለው ሰላም ዘላቂ እንዲሆንና ሀገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ህዝብን ወደአንድ በሚያመጡ ተግባራት ላይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚንቀሳቀሱም አመልክተዋል።

የከተማ አስተዳዳሩ ከንቲባ አቶ አህመድ ሀጂ በበኩላቸው ” የኮንፈረንሱ  ዓላማ በከተማችን የሚኖሩ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እንደከዚህ ቀደሙ ያለስጋት በእኩልነትና በፍቅር ተባብረው እንዲኖሩ ማስቻል ነው” ብለዋል፡፡

ከተማዋን ለነዋሪዎች ተስማሚና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ማዕከል በማድረግ ዕድገቷን ለማቀላጠፍ መንግስት እያደረገ የሚገኘውን ጥረት ህዝቡ እንዲያግዝ ጠይቀዋል፡፡

" ዜጎች ሰላም ለሰው ልጆች ያለውን መተኪያየለሽ ሚና በመረዳት ሰላማቸውን ለማስከበርና ለአንድነታቸው በጋራ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል” ያሉት ደግሞ የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሀጂ ናቸው፡፡

አስተዳዳሪው እንዳሉት በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ የማይፈልጉ አካላት በየቦታው የብሔርና የሃይማኖት መልክ ያላቸው ግጭቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ በህዝቦች መካከል መተማመን እንዳይኖር ሌተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በጎባ ከተማና አካባቢዋ ከአምስት ወራት በፊት ህዝቡን በብሔርና ሃይማኖት ለመለያየት የተደረገው ጥረት ለጊዜው ጉዳት ቢያስከትልም በሰላም ወዳዱ ህዝብ ሊከሽፍ መቻሉን አስታውሰዋል፡፡

"ለውጡን የማይፈልጉ ኃይሎች በተለይ ህገ መንግስታዊ መልስና ዋስትና ጭምር ካገኘ ዓመታት ያስቆጠረውን የኦሮሞ ህዝብ ባህሉንና ቋንቋውን የማሳደግ መብቶችን እንደ ሽፋን በመጠቀም አብሮነትን ለመፈታተን ሲጥሩ ይታያል" ብለዋል፡፡

የዞኑ ህዝብ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ በመጠበቅ በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ፍሬ እንዲያፈራ ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የትምህርትና ቴክኒክ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤባ ገርባ በበኩላቸው “  የክልሉ መንግስት የህዝቡን ሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ በሀገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ መጠበቅና ዳር ማድረስ ቀዳሚ አጀንዳው ነው" ብለዋል፡፡

ህዝቡም በስሙ የሚነግዱ አጥፊዎችን መንጥሮ በማውጣት ሰላምን አስተማማኝ ማድረግና ፊቱን ወደ ልማቱ መመለስ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በከተማዋ የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር ለመመለስ ጥረት ላደረጉ የሃይማኖት አባቶች፣ ቄሮዎች፣ የአገር ሸማግሌዎችና ለአስታራቂ ኮሚቴ አባላት እውቅና ተሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም