በአዲስ አበባ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ለተጠቃሚዎች 800 ሚሊዮን ብር ብድር ሰጡ

61

አዳማ ጥር 9/2011 የአዲስ አበባ ከተማ ብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች ባለፉት ስድስት ወራት ለተጠቃሚዎች ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መስጠታቸውን የከተማዋ ህብረት ሥራ ኤጄንሲ ገለጸ።

በከተማዋ በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ህይወት ለማሻሻል ማህበራቱ አማራጭ  የፋይናንስ ምንጭ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውን የኤጄንሲው  ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው አሊ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በሰጡት የብድር ገንዘብ ከ180 ሺህ በላይ ዜጎች በተለያዩ የሥራ መስክ እንዲሰማሩ መደረጉን አመልክተዋል።

ዋስትና ማስያዝ የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆን የሚችሉበት አሰራር በማመቻቸት ጭምር የብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት የዜጎችን ህይወት በመለወጥ ረገድ  ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ተናግረዋል።

የስድስት ወራት አፈፃፀም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለማሰራጨት ታቅዶ ክንውኑ  80 በመቶ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀሪዎቹ ስድስት ወራት ከ1 ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ በብድር ለማሰራጨትና ከ220 ሺህ በላይ የሚሆኑ  ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው የታቀደው፡፡

የበጀት ዓመቱን እቅዳችን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ዘመናዊ አሰራርና አደረጃጀትን ጨምሮ አዲስ የብድር አገልግሎት አሰጣጥ ሶፍት ዌር በመዘርጋት ወደ ሥራ ተገብቷል ።

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት እቅድ ሙሉ በሙሉ ማሳካት ያልተቻለው የከተማዋን የብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት አሰራር ለማዘመን፣ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ሪፎርም ሲከናወን በመቆየቱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ዳይሬክተሩ " በአሁኑ ወቅት በአዲሱ የብድር አገልግሎት አሰጣጥና ክፍያ ሶፍት ዌር በመታገዝ የተቀላጠፈ አገልግሎት እየሰጠን ነው" ብለዋል።

በተመሳሳይ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ ለማሰባሰብ ግብ አስቀምጠው እየሰሩ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግዛቸው እስካሁንም 1 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በቁጠባ ማሰባሰብ እንደቻሉ አስታውቀዋል።

የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ደመወዝ አወቀ በሰጡት አስተያየት  ባገኙት የብድር ገንዘብ የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ማምረቻና ማከፋፈያ ድርጅት በመክፈት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አገልግሎት በማግኘት የማስፋፊያ ሥራና የድርጅቱን አቅም የማጠናከር ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

"በዚህም በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ በመሆን የካፒታል አቅማችን ከ4 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ማድረስ ችለናል " ያሉት አቶ ደመወዝ የድርጅታቸው ሠራተኞች እርስ በርሳቸው አንዱ ለሌላው ዋስ በመሆን  የብድር አገልግሎት እንዲያገኙና ሠርተው መለወጥ እንዲችሉ ጭምር እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በከተሞች የድህነት ቅነሳ ፕሮግራም ውስጥ የገንዘብ ብድርና ቁጠባ ማህበራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኘው ህብረተሰብ አነስተኛ ፋይናንስ በማቅረብ ረገድ እየተጫወቱ ያሉት ሚና የላቀ መሆኑን  የገለፁት ደግሞ የፌዴራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲ ሙሐመድ ናቸው ።

"ፍትሃዊ የፋይናንስ ተደራሽነትና ተጠቃሚነትን በየደረጃው ማረጋገጥ ላይ የብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት እያከናወኑ ያሉት ተግባራት አበረታች ነው "ብለዋል።

በሀገሪቱ ዜጎች እንደ አቅማቸው የሚቆጥቡበትና የብድር አገልግሎት የሚያገኙበት ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል የሚያንቀሳቅሱ ከ17 ሺህ በላይ የብድርና ቁጠባ ህብረት ሥራ ማህበራት  እንደሚገኙ አመልክተዋል።

አቶ አብዲ እንዳሉት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ሰፊው ህብረተሰብ ዘንድ በፍትሃዊነት እንዲደርሱና ሁሉም ዜጋ  በየደረጃው ተጠቃሚ እንዲሆን ዘመናዊ አሰራር ከመዘርጋት ጀምሮ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም