የንግድ አሰራር ወጥነት አለመኖርና የግብዓት አቅርቦት ማነስ ግብር በወቅቱ እንዳንከፍል አድርጎናል- በደሴ ግብር ከፋዮች

108

ደሴ ጥር 9/2011 የንግድ አሰራር ወጥነት አለመኖርና የግብዓት አቅርቦት ማነስ ግብር በወቅቱ እንዳይከፍሉ እንዳደረጋቸው የደሴና አካባቢው የፌደራል ግብር ከፋዮች ገለጹ፡፡

በከተማው በንግድ አሰራርና በግብዓት አቅርቦት ችግሮችና መፍትሄዎች ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ግብር ከፋዮቹ በዚሁ ወቅት በንግድ አሰራር ላይ  ወጥነት ያለው አሰራር ማጣትና የግብዓት አቅርቦት ችግር ግብር በወቅቱ እንዳንከፍል አድርጎናል ብለዋል፡፡

የወሎ ምግብ ኮምፕሌክስ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ መሐመድ ከግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ የፌዴራልና የክልል የአሰራር መመሪያዎች መለያየት በስራቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ፋብሪካው በወር 35 ሺህ ኩንታል ስንዴ የመፍጨት አቅም ቢኖረውም፤ከመንግሥት በድጎማ የሚቀርብላቸው ስንዴ አራት ሺህ ኩንታል ያህል መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል።

ከአምራቾችና ነጋዴዎች ስንዴ ለመግዛት ቢፈልጉም፤ ሻጮቹ ደረሰኝ ስለማያቀርቡ የአሰራር ክፍተት መፍጠሩንም ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ የክልል ግብር ከፋዮች ያለ ደረሰኝ እየተጠቀሙ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አሰፋ፣ ይሄም  በገበያ ተወዳዳሪና ተጠቃሚ እንዳይሆኑ ማድረጉን  አብራርተዋል።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ላኮመንዛ ንግድና ማማከር ሥራዎች ኢንተርፕራይዝ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረጀ አሳምነው በሽያጭ መመዝገቢያ ወረቀት እጥረት በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

የወሎ ህንጻ አከራይ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስኪያጅ  አቶ ተስፋዬ ይመር በበኩላቸው የገቢዎች ሚኒስቴርና የደሴ ከተማ አገልግሎት ጽህፈት ቤት አሰራር በመለያየቱ 500 ሺህ ብር የተገመተውን የህንጻ የስም ዝውውር ለማስፈጸም 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

በፌዴራል ገቢዎች ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያረጋል ኃይሉ በጉዳዩ ላይ ከአማራ ክልል ገቢዎች ጽህፈት ቤትና ከደሴ ከተማ አስተዳደር ጋር በተደረገው ውይይት "በነጋዴዎች ሥራ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ ያሉ የአሰራር ልዩነቶች  እንደገና እንዲታዩ ተወስኗል" ብለዋል፡፡

ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን በመለየት ወደ ሕጋዊ አሰራር ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያስረዱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ሕጋዊ በማይሆኑት ላይ  እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል፡፡

በከተማው ባለፉት ስድስት ወራት ከግብር ከፋዮች ለመሰብሰብ የታቀደው 856 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፤የተሰበሰበው 370 ሚሊዮን ብር መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም