በዓሉ የክልሉ ነዋሪዎችን ባህልና እሴቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ ይከበራል

40

ሐረር ጥር 9/2011 የሐረሪ ክልል ነዋሪዎችን ባህልና እሴቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ የጥምቀት በዓል እንደሚከበር የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።

በዓሉ ያለአንዳች የጸጥታ ችግር ለማክበር ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እንደሚሰሩ በከተማው የሚገኙ ወጣቶች ተናግረዋል።

የክልሉ ፍትህና ጸጥታ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ዩሱፍ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በዓሉ የነዋሪዎችን በሰላም፣በመቻቻል፣ በመረዳዳትና አብሮነት በሚያንጸባርቅ መልኩ ይከበራል።

የክልሉ ነዋሪዎች የትኛውንም ሐይማኖታዊ በዓል በጋራ የሚያከብሩበት ባህል እንዳላቸው አመልክተው፣ጥምቀትም ይህንኑ የቆየ እሴትና ባህል ጠብቆ እንደሚከበር ተናግረዋል።

ለዚህም የክልሉ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ፣የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች በዓሉን ለማክበር መዘጋጀታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።

የክልሉ የሐይማኖት ተቋማት ጉባዔ አስተባባሪ አቶ አበበ አራርሳ ጉባዔው በዓሉን በጋራ እንደሚያከብሩት  አስታውቀዋል።

ቢሮው ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንዲከበር  ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር  ተቀናጅቶ  እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምሥራቅ ሐረርጌ አገረ ስብከት ጸሐፊ ሊቀ ህሩያን ፍሰሀጽዮን አደመ በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በተከተለ መንገድ በድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በዓሉ የክልሉ እሴቶች የሆኑት አብሮነትና መደጋገፍ የሚንጸባረቅበት በመሆኑ በዓሉ ልዩ ቦታ እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

''በዓሉ ያለአንዳች የጸጥታ ችግር ለማክበር ከጸጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እንሰራለን'' ያለው የሐረር ከተማ ነዋሪው ወጣት ይትባረክ መላኩ፣ የበዓሉ ዝግጅት ሁሉንም ወጣቶች ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ወጣት አደም ሀሰን  በበኩሉ “ ለሦስት ቀን በሚቆየው በዓል የምዕመናኑን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሥራዎችን ተከፋፍለን እየሰራን እንገኛለን። በዓሉንም አብረን እናከብራለን” ብሏል።

የጥምቀት በዓል የፊታችን ቅዳሜ በመላ ኢትዮጵያ በተለይ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ ይከበራል።

በበዓሉ ዋዜማ ነገ በሚከበረው የከተራ በዓል ታቦታት በምዕመናን ታጅበው ከየአብያተ ክርስቲያናት ወጥተው ወደ ማደሪያቸው ­ጥምቀተ ባህር ይሰባሰባሉ።

ኢትዮጵያ ጥምቀትን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ እንቅስቃሴ እያደረገች ናት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም