በደቡብ ክልል የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች እና የባህል ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው

166

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች ክልል የትንፋሽ ሙዚቃ መሣሪያዎች (ፊላ) እና የባህል ፌስቲቫል ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሄድ ነው፡፡

በክልሉ ሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የደራሼ ወረዳ አስተዳደር ያዘጋጀው የፊላ እና የባህል ፌስቲቫል ከጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶስት ቀናትይካሄደል፡፡

ፌስቲቫሉ በተለይ ከኢትዮጵያ የባህል የትንፋሽ የሙዚቃ መሣሪያዎች መካከል ባለብዙ ኖታ በመባል የሚታወቀውና በአቀራረብ ስልቱም የሚለየው 'ፊላ' የተሰኘው መሳሪያ እንዲታወቅ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ካሳሁን አያሌው ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፌስቲቫሉ በወረዳው የሚታወቁ አስደናቂ ባህላዊና ትውፊታዊ ሥነ ሥርዓቶች በአገሪቱም ሆነ በሌላ የዓለም ክፍል እንዲተዋወቁም ያደርጋል፡፡

ባህልን፣ ቅርስንና ታሪክን ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ ደግሞ እንደነዚህ ያሉ መርሃ ግብሮች ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ነው የገለጹት፡፡

እንዲሁም በሥነ ሥርዓቱ ላይ በክልሉ ለ20 ዓመታት ያህል እህል ሳይበላሽ የሚቀመጥበት ጎተራና የክልሉ ባህላዊ ትውፊቶች ይጎበኛሉ፡፡

በተጨማሪም በፌስቲቫሉ የማህበረሰቡ ዋና መገለጫ የሆኑት የደራሼ የፊላ ሙዚቃ እና የሴቶች ጨዋታ፣ ልጃገረዶች፣ ወጣቶችና አዋቂዎች የሚለብሷቸው የተለዩ ባህላዊ አልባሳት እና የተለያዩ ጭፈራዎች በየአደባባዮችና በየጎዳናዎች ይታያሉ፡፡

በፌስቲቫሉ ላይ የሚኒስቴሩ ተወካዮች የክልሉ ባለሥልጣናትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም