የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ በምክር ቤት ጸደቀ

79

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሁለት ቋሚ ኮሚቴዎች በስደተኞች ጉዳይ ላይ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምጽ አጸደቀ።

የምክር ቤቱ የህግ ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች እና የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በስደተኞች ጉዳዮች ላይ ያቀረቡትን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አድምጧል።

የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በዚህ ጊዜ እንደገለጹት አዋጁ ኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ የምታስተናግድበት አዋጅ በዝርዝር ያልሸፈናቸውን ጉዳዮች ለማካተት ያለመ ነው።

በተለይም አሁን ያለውን ዓለም ዓቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ሁኔታዎችን በመቋቋምና በማስተናገድ የአገሪቷን ዜጎችና ስደተኞችን በጋራ ለማልማት የሚያስችል ዝርዝር የህግ ማዕቀፍ ማበጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ስለሆነም በኢትዮጵያ ከለላ ያገኙና ጥያቄ ያቀረቡ ስደተኞች በሚገኙበት አካባቢ ማህበረሰብ ጋር ተዋህደው የአገሪቷን የሊዝና የፋይናንስ አሰራር መሰረት ባደረገ መልኩ በልማት የሚሰማሩበት አሰራር እንዲዘረጋ ያስችላል። 

አዋጁ አገሪቷ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነትና ተቀባይነት ከፍ ለማድረግ፣ ስደተኞች በሚኖሩበትና ሌሎች አካባቢዎች በተሻለ ሁኔታ የልማት ተግባር እንዲያከናውኑ የሚያደርግ መሆኑን ወይዘሮ ፎዚያ ጠቁመዋል።

በዚህም ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር፣ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠርና በኢትዮጵያ የስደተኞች አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን ለማሻሻል ያስችላል ሲሉ አብራርተዋል።

ምክር ቤቱም የአዋጁን ማብራሪያ ካደመጠ በኋላ በሶስት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም