ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ በኮንጎ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር አዲስ አበባ ገቡ

84

አዲስ አበባ ጥር 9/2011 የሩዋንዳ ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ህብረት ሊቀ-መንበር ፖል ካጋሜ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረውን አስቸኳይ ስብሰባ ለመምራት አዲስ አበባ ገቡ።

ሊቀ-መንበሩ በጠሩት አስቸኳይ ስብሰባ የደቡብ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (ሳድክ) 16 አባል አገራት መሪዎች እንደሚሳተፉና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ እንደሚመክሩ የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል።

ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚካሄድ ሲሆን የውይይቱ ዝርዝር ጉዳይ አልተገለጸም።

ታህሳስ 21 ቀን 2011 ዓ.ም ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ማድረጓ ይታወሳል።

የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን ታህሳስ 25 ቀን 2011 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ውጤት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ፌሊክስ ሺሰኬዲ ሺሎምቦ ተፎካካሪያቸውን ማርቲን ፋዩሉ እንዳሸነፉና ፕሬዝዳንት እንደሆኑ ገልጾ ነበር።

በምርጫው የተሸነፉት ማርቲን ፋዩሉ የምርጫው ውጤት የተጭበረበረ ነው አልቀበለውም ውጤቱ "የምርጫ መፈንቅለ-መንግስት" ነው የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላና ፌሊክስ ሺሰኬዲ ሺሎምቦ ተመሳጥረው ባደረጉት ስምምነት ነው የተሸነፍኩት ማለታቸው አይዘነጋም።

በዚህም በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የፖለቲካ ውጥረት እንደነገሰ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ይገኛሉ።

የአፍሪካ መገናኛ ብዙሃን ከዲፕሎማት ምንጮች አገኘነው ባሉት መረጃ  ፖል ካጋሜና የደቡብ አፍሪካ የልማት ማህበረሰብ (ሳድክ) አባል አገራት መሪዎች የሚያደርጉት ውይይት ያለውን ውዝግብ በመፍታት ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው።

የሳድክ አባል አገራት መሪዎች ከፖል ካጋሜ ጋር ውይይት ከማድረጋቸው በፊት የአባል አገራቱ መሪዎች የራሳቸውን ውይይት እንደሚያደርጉም ታውቋል።

በታህሳስ 2010 ዓ.ም የተደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ኮንጎ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር 1960 ነጻነቷን ካገኘች ወዲህ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለመረካከብ የመጀመሪያው ምርጫ መሆኑ ይታወቃል።

ጆሴፍ ካቢላ ላለፉት 17 ዓመታት አገሪቱን መምራታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም