የ‘ኮፊ አራቢካ’ የቡና ዝርያ የመጥፋት አደጋ ገጥሞታል

74

ጥር 9/2011 ኢትዮጵያ በዋነኝነት ለውጭ ገበያ እያቀረበችው የሚገኘው ‘ኮፊ አራቢካ’ የተሰኘው የቡና ዝርያ የመጥፋት አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ በእንግሊዝ ሃገር የተደረገ ጥናትን ዋቢ ያደረገው ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
እንደ መረጃው አራቢካን ጨምሮ 60 በመቶ የሚሆኑት የጫካ ቡና ዝርያዎች የመጥፋት አደጋ አንዣቦባቸዋል።
ላለፉት ሁለት አስርተ አመታት በእንግሊዛውያን የዕፅዋት አጥኚ ሳይንቲስቶች የተደረገው ጥናት ያመለከተው በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየበቀለ የሚገኘው አራቢካ የተሰኘው የቡና ዝርያ ብዛት እኤአ በ2080 በ85 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ነው።
በምዕተ አመቱ መጨረሻም 60 በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ የቡና ምርትና አይነት ለተጠቃሚው ተስማሚ እንደማይሆንም ሳይንቲስቶቹ ተናግረዋል። በርካቶቹ የቡና ዝርያዎች በአፍሪካና ማዳጋስካር ጨካዎች እንደመገኘታቸው በአየር ንብረት መዛባት፣ በዕፅዋት ቁጥር መቀነስ ብሎም በተለያዩ የዕፅዋት በሽታዎችና ተባዮች አማካይነት የመጥፋት አደጋ እንደተጋረጠባቸው ሳይቲስቶቹ ያካሄዱት ጥናት አመልከቷል።
በአለም አቀፍ ደረጃ የቡና ተፈላጊነት እና አትራፊነት እንዲሁም በብዛት አምርቶ መጠቀሙ እያደገ መምጣት የዕፅዋቱን ጤና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ብሎም በአየር ንብረት መዛባት እንዲጠቃ ያደርገዋል ብሏል ለሃያ አመታት የተካሄደው ጥናት።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ ቡና ላኪ ሀገር መሆኗን ያነሳው ዘ ጋርዲያን ከምትልከውም ቡና በያመቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደምታገኝ ጠቅሷል።
የሃገሪቱ 15 ሚሊዮን የሚሆነው ዜጋም በቡና ማምረት ተግባር ላይ እንደተሰማራና በብዛትም የጫካ አራቢካ ቡና እያመረተ እንደሚገኝም መረጃው አትቷል።
ስለሆነም በአራቢካ ቡና ዝርያ ላይ የተጋረጠው የመጥፋት አደጋም የሃገሪቱን ምጣኔ ሃብት ክፉኛ ሊጎዳው እንደሚችል ማሰቡ ቀላል እንደሆነም ዘ ጋርዲያን አንስቷል። የጫካ ቡና የመጥፋት አደጋ ውስጥ መገኘት የአለም አቀፉን የቡና ገበያ ሊጎዳው እንደሚችል ያነሱት ሳይንቲስቶቹ የአየር ንብረት መዛባቱም ሆነ የዕፅዋት በሽታዎችን ለመከላከል የሚያስችሉ ስራዎች መሰራት እንደሚገባቸው መክረዋል።
የእንግሊዝ ሮያል ቦታኒክ ጋርደን ሳይንቲስቶች 124 የቡና ዝርያዎችን መርጠው ያካሄዱትን ጥናት ‘ሳይንስ አድቫንስስ ኤንድ ግሎባል ቼንጅ ባዮሎጂ’ በተሰኘ ጆርናል ላይ እንዲታተም ማድረጋቸውንም ዘጋርዲያን ይዞት ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም