በምዕራብ ጉጂ ዞን አንጻራዊ ሰላም መስፈኑ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ

66

ነገሌ ጥር 9/2011 በምዕራብ ጉጂ ዞን አንጻራዊ ሰላም በመስፈኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው እየተረጋጋ መምጣቱ የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ።

የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ለዘላቂ ሰላም መስፈን የህግ የበላይነት እንዲከበር ጠይቀዋል።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በዞኑ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር የመማር ማስተማሩን ሥራ ከማስተጓጎል ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል።

አስተዳደሩ በአባገዳዎች ሰብሳቢነት ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት ጋር መወያየት በመቻሉም በአሁኑ ወቅት በአካባቢው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን  ጠቁመዋል።

በዞኑ በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና በሁለት ከተሞች የተካሄደውን የሰላም ውይይት ተከትሎ ተዘግተው የነበሩ 33 ትምህርት ቤቶች ተከፍተው ማስተማር መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በፀጥታ ችግር አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የመሰረተ ልማት ተቋማትም በአብዛኛው ሥራ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

በዱግዳ ዳዋና ቡሌ ሆራ ዙሪያ ወረዳ ያልተከፈቱ አንዳንድ ትምህርት ቤቶችን ሥራ ለማስጀመር  በአሁኑ ወቅት ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑንም አቶ አበራ አመልክተዋል፡፡

"በአባገዳዎች የታወጀው የሰላም ሳምንት በዞኑ የነበረውን የፀጥታ ችግር በማቃለል የተረጋጋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲሰፍን አድርጓል" ብለዋል፡፡

የቡሌ ሆራ ከተማ ነዋሪ አቶ ጃተኒ በሪሶ በበኩላቸው በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግር እሳቸውን ጨምሮ ህዝቡን ለስጋትና ጭንቀት ዳርጎ እንደነበር አስታውሰው ለዞኑ ሰላም መስፈን አባገዳዎች ላበረከቱት አስታዋጽኦ አመስግነዋል።

ለአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም መስፈን የህግ የበላይነት እንዲከበር ጠይቀው ለእዚህም የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ ሩዳ ጠሮ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው " በአበገዳዎች፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የተላለፈውን የሰላም ጥሪ ሁላችንም ተቀብለን ችግሮቻችንን በውይይት ብቻ ልንፈታ ይገባል" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየታየ ያለው አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥም መንግስት የጀመረውን ህግ የማስከበር ሥራ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል። 

በጉጂ ዞን በአሁኑ ወቅት ሰላም በመስፈኑ 592 ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ተግባራቸውን በአግባቡ እየተወጡ ይገኛሉ።

በትምህርት ቤቶቹ ከ300 ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎችም መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ከዞኑ የተገኘውን መረጃ ዋቢ አድርጎ የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም